ዋሽንግተን ዲሲ —
የፓኪስታን ባለስልጣናት ባለፈው ዕሁድ ላሆር ከተማ ውስጥ የሚበዙት የእየሱስ ክርስቶስ ትንሳዔ በዓልን በማክበር ላይ የነበሩ ክርስቲያኖች የሆኑ ቢያንስ ሰባ ሁለት ሰዎች ከገደለው አጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ተከትሎ በያዙት ከባድ ርምጃ ከሁለት መቶ በላይ እስላማዊ ጽንፈኞችን አስረዋል።
በሃገሪቱ በህዝብ ብዛት አንደኛ በሆነችው በፑንጃብ ክፍለ ሃገር ዋና ከተማ ላሆር ህዝብ የታጨቀበት መናፈሻ ላይ በደረሰው ፍንዳታ ከሞቱት መካከል ሃያ ስምንቱ ህጻናት ሲሆኑ ከሶስት መቶ የሚበልጡ ቆስለዋል።
የፓኪስታን ፖሊሶችና ልዩ የጸረ ሽብርተኛ ክፍሎች በደህንነት መኮንኖች እየተመሩ በመላዋ ፑንጃብ አሰሳ አካሂደው ከአምስት ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን ማሰራቸውን የክፍለ ሃገሩ የህግ ሚኒስትር ራና ሳናሁላህ ገልጸዋል።
ከዚያም ሁለት መቶ አስራ ስድስቱን ብቻ ለቀጣይ ምርመራ አስቀርተው የተቀሩትን ለቀዋቸዋል። ከፓኪስታኑ ታሊባን የተገነጠለው ጃማቱል አህራር ለጥቃቱ ሃላፊነት የወሰደ ሲሆን ሆን ብሎ ክርስቲያኖችን ዒላማ አድርጎ የወሰደው ርምጃ መሆኑን አስታውቋል።