የመንግሥት ኃይሎች ኦሮሚያ ውስጥ እየወሰዱ ያሉት እርምጃ “እጅግ አስከፊ” ወይም በእንግሊዝኛው ቀጥተኛ አባባል “ብሩታል” ናቸው ሲል ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አውግዟል። እርምጃዎቹ ሁኔታውን ከማባባስ በስተቀር የሚፈይደው የለም ብሎታል፡፡
በጉዳዩ ውስጥ የተሣተፉ ወገኖች ሁሉ ከአመፃና ከሁከት አድራጎት መቆጠብና ድምፆቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ቢያሰሙ እንደሚበጅም ቡድኑ መክሯል፡፡
የዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International) ከትናንትና ወድያ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያ ክልል የተነሳው ተቃውሞ ሰልፍ ላይ የወሰደውን የሃል እምርጃ ኮንኗል። መንግስት የኢትዮጵያን ጸረ-ሽበር ህግን በመጥቀስ “ሰልፈኞቹ ከውጭ በሚያገኙት ድጋፍ የኢትዮጵያን ሰላም ለማወክ የጀመሩት ሁከት ነው” ያለውን አምነስቲ መግለጫ አጣጥሎታል።
እስካሁን የመንግሥት ባለስልጣናት አምስት ሰዎች ተገድለዋል ሲሉ፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ዋና ጸሐፊ አቶ በቀለ ነጋ በበኩላቸው ከ40 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህወታቸውን ማጣታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የኮሚውኒኬሽንስ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው 4 ፓሊሶች መገደላቸውን ከዚህ በፊት መግለጻቸው ይታወሳል።
የመንግሥት ኃይሎች ኦሮሚያ ውስጥ እየወሰዱ ያሉት እርምጃ “እጅግ አስከፊ”ናቸውዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን አምነስቲ ኢንተርናሽናል
አዶቴይ አክዌ ኒው ዮርክ ያሉትን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዩኤስኤን (USA) ከመንግሥት ጋር ያሉ ግንኙነቶች ዋና ዳይሬክተር ናቸው። የኢትዮጵያ የኮሚውኒኬሽንስ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ያነሱትን የውጭ ድጋፍ ምክንያት እንዴት እንደሚመለከቱት፣ በእአአ በ2014 በተከሰተው ሰልፍ ህወታቸውን ያጡ ዜጎች ፍትህ ባለማግኘታቸው እና እስካሁን በተጠያቂነት የቀረበ አካል ባለመኖሩ ያላቸውን ሃሳብ እንዲያካፍሉን ጠይቀናቸው ነበር።
በተጨማሪም አዶቴይ አክዌ በአሁኑ ሁኔታ ለውጥ ይኖራል ብለው ለምን ይጠብቃሉ ብለን በጠየቅናቸው ጥያቄ የሰጡትን መልሶች ሳሌም ሰለሞን አነጋግራ ተከታዩን አጠናቅራለች፡፡ ከዚህ በታች ያለውን የድምጽ ፋይል በመጫን ያዳምጡ።