እስላማዊ መንግሥት ነኝ ባዩ ነውጠኛ ቡድን ጥቃት የሚፈጽምባቸውና አሰቃቂ ወከባ የሚያካሂድባቸው ጦር መሣሪያዎች ብዙዎቹ የተገኙት ከኢራቅ ወታደራዊ ጥቅንና ስንቅ ክምችት ውስጥ መሆኑን ዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International) አስታወቀ። “ይህ ደግሞ” አለ ድርጅቱ፣ “ሰላማቸው ወዳልተረጋገጠ አገሮች ጦር መሣሪያ ለመላክ ጥንቃቄን ይፈልጋል” ብለዋል።
አምነስቲ፣ ቢሮውን አውስትሬሊያ ውስጥ ያደረገው የጦር መሣሪያ መቆጣጠሪያ አገልግሎት ትናንት ማክሰኞ ይፋ ያደረገው መግለጫ መሰረት በማድረግ እንዳመለከተው፣ ሦርያና ኢራቅ ውስጥ አገልግሎት ላይ የዋሉ ጦር መሣሪያዎች ተመርምረው፣ ከ23 አገሮች የተገኙ መሆናቸው ተደርሶበታል። ጦር መሣሪያዎቹ በከፍተኛ ደረጃ የተላኩት ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከሩስያና ከቀድሞዋ ሶቭዬት ሕብረት ነው።
አምነስቲ፣ ሌሎች የሰባዊ መብት አስጠባቂ ቡድኖችና የተመድ በጋራ መግለጫቸው፣ እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው አማጺ ቡድን፣ ጦር መሣሪያዎችን ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ከመጠቀሙም ባሻገር፣ እንደ አስገድዶ መድፈር፣ ሰቆቃ፣ ወከባና እገታ የመሰሉ ወንጀሎችን እንደሚፈጽም አመልክተዋል።
ይህ ነውጠኛ ቡድን ካለፈው ዓመት ኣጋማሽ ጀምሮ ምሥራቃዊ ሦርያን፤ ሰሜንና ምዕራባዊ ኢራቅን ከተቆጣጠረ ወዲህ፣ በብዙ መቶ ሺህዎች የሚቆጠር ሕዝብ ከቤር ንብረቱ መፈናቀሉም ታውቋል።
አንድ የተመድ የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ውይይት ይፋ እንዳደረገው፣ ቡድኑ አብዛኛውን ጦር መሣሪያ በእጁ ያስገባው እአአ ከሰኔ 2014 መወዲህ ነው።