በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"ወጣቱ ይህ መንግሥት በሚያደርገው ነገር ሁሉ ተንገሽግሿል"ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና


በማልታ የሚገኙ የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም ለተቃውሞ ሰልፍ በወጡበት ወቅት-ፎቶ ፋይል፡(ሮይተርስ)
በማልታ የሚገኙ የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም ለተቃውሞ ሰልፍ በወጡበት ወቅት-ፎቶ ፋይል፡(ሮይተርስ)

ላለፉት ሦስት ሳምንታት የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት ተማሪዎች የአዲስ አበባ እና የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተግባራዊ ይደረጋል መባሉን ሲቃወሙ ሰንብተዋል። የተቃውሞውን ጅምር የሚያትተውን የማርታ ፋን ደር ቮልፍ የአዲስ አበባ ዘገባ ጨምራ፤ ጽዮን ግርማ የዛሬዉን የተቃውሞ ሰልፍ ውሎ የተመለከት ርእሶችን ይዛለች፡፡

የተቃውሞው መነሻ "ያለ ተገቢ የገንዘብ ክፍያ ገበሬዎችን የሚያፈናቅል የመሬት ቅርምት ነዉ" የሚል መኾኑ ሲዘገብ ቆይቷል። የጸጥታ ኃይሎች ሰልፈኞቹ ላይ በወሰዱት ርምጃ ቢያንስ አምስት ሰዎች እንደተገደሉ መንግሥት አምኗል። የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች በበኩላቸው የተገደለዉ ሰዉ ቁጥር ስልሳ እንደሚደርስ ተናግረዋል፡፡ የጸጥታ አስከባሪዎች ሕይወት ማለፉም ተገልጿል።

የኦሮመኛ ቋንቋ ዝግጅት ክፍል ባልደረቦቻችን ስለ ዛሬው የተቃውሞ ሰልፍ ውሎ ምንጮቻቸውን ጠቅሰው እንደዘገቡት፤በዛሬው ዕለት በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ ፣በሱሉልታ፣ በሆሮ ጉድሩ፣በነጆ፣በጫንቃና በሌሎች ቦታዎች ሰልፉ መቀጠሉንና በዚሕም የሰው ሕይወት መጥፋቱ ተገልጿል፡፡

ማስተር ፕላኑ መሰረዝ አለበት፡፡የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም ፈርሶ በሌላ መተካት አለበት
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ መሪ

በሌላ በኩል በኢሉባቡር አልጌ ሳቺ ከተማ ለሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ተቃውሟቸውን አሰምተው በሰላም መመለሳቸው ታውቋል፡፡ በተጨማሪም ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች መታሰራቸውን አብዛኞቹ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በፌደራልና መከላከያ ፖሊስ ጥብቅ ጥበቃ ሥር መዋላቸውን ዘግበዋል፡፡

በሌላ በኩል ማርታ ከአዲስ አበባ ባጠናከረችው ዘገባ "የተማሪዎቹ ተቃውሞ ወዲያዉ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ክልልን አዳረሰ፡፡" ሲል ይጀምራል፡፡ ገበሬዎችና ሌሎች ነዋሪዎችም በተቃውሞዉ ተማሪዎቹን ተቀላቀሉ። መንግሥት አንዳንዶቹ ተቃዋሚዎች አገሪቱን ለማናጋት የሚንቀሳቀሱ ናቸዉ በማለት ይከሳል። ለደህንነታቸዉ በመስጋት ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የክልሉ ነዋሪ፤ወደ ክልሉ የተላኩ የጸጥታ ኃይሎች ሌሎች ሰዎች ተቃውሞውን እንዳይቀላቀሉ መንገዶችን ዘግቶ እየተቆጣጠረ እንደኾነ ተናግረዋል።

እንደ ነዋሪው ገለፃ “አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች ገበሬዎች ናቸዉ። ከገጠር አካባቢዎች ነው ወደ ከተሞች የሚመጡት። የመከላከያ ኃይል ደግሞ ወደ እነዚህ ገጠሮች አምርቷል። ፖሊሶችም ተቃዋሚ ሰልፈኞቹን ቁጥጥር ስር እያዋሉ ነዉ።”

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር ባደረጉት ግጭት አምስት ሰዎች መሞታቸዉን አረጋግጫለሁ ብሏል፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 60 ደርሷል ይላሉ። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽል (Amnesty International) ትላንት ዕረቡ ባወጣዉ መግለጫ መንግሥት ተቃውሞዉን በኃይል እያፈነ ነዉ ብሏል።

በአዲስ አበባና ዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተባለውን በመቃወም ባለፈዉ ዓመት ሚያዚያ ወርም እንዲሁ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር። ተቃውሞዉን ተከትሎ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል ርምጃ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ሰዎችም ታስረዋል። ማስተር ፕላን የተባለዉ የዋና ከተማዋን ማለትም የአዲስ አበባን ድንበር የሚያሰፋ ንድፍ ነዉ። በዙሪያዋ የሚኖሩ የኦሮሚያ ክልላዊ አስተዳደር ዜጎች "የታቀደው መዋቅር መሬታችንን ነጥቆን የባህል ቅርሶቻችንን የሚያወድም በመኾኑ ያሳስበናል" ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ካለፈዉ ዓመት ተቃውሞ በኋላ ስለ ማስተር ፕላኑ ጉዳይ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ሁለገብ ዉይይት ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር። ተቃዋሚው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ መሪ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እነዚያ ቃል የተገቡት ውይይቶች አልተደረጉም ይላሉ።

"ብዙ ጊዜ ውይይት እንዲደረግ ሞከርን፣ አናደርግም አሉ። ከዚያም ግልጽ ሕዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ሞከርን እሱንም እንቢ አሉ። መንገዱን ዘጉብን። አሁን እንግዲህ እዚህ ላይ ደረስን። የዚህ መንግሥት ሁኔታ ሕዝቡን አንገሽግሾታል። በተለይም ወጣቱ ይህ መንግሥት በሚያደርገው ነገር ኹሉ ተንገሽግሿል።"ሲሉ ይገልጻሉ፡:

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ፤ "ማስተር ፕላኑ መሰረዝ አለበት፡፡የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም ፈርሶ በሌላ መተካት አለበት"ይላሉ። መንግሥት በበኩሉ ማስተር ፕላኑ ሥራ ላይ አልዋለም ይላል፤ ተቃዋሚዎች ደግሞ ገበሬዎችን ማፈናቀል ከተጀመረ እንደቆየ ይገልጻሉ።

በኢትዮጵያ ብዙም ተቃውሞ አይካሄድም። ገዢዉ ፓርቲ እንደ አዉሮፓውያን አቆጣጠር በ1991 ዓ.ም ሥልጣን የያዘ ሲኾን ባለፈው ግንቦት ወር በተካሄደ ምርጫ ሙሉውን የምክር ቤት መቀመጫ ተቆጣጥሯል። የጸጥታ ጥናቶች ተቋም ባልደረባ ሃሌሉያ ሉሌ ውጥረት እንደሰፈነ ይናገራል።

"ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ተቃውሞ እየተመለከትን ነዉ። የጸጥታ ኃይሎቹም ኾነ መንግሥት የተከሰተዉን ከፍተኛ ተቃውሞ የጠበቁ አይመስለኝም። በእኔ እምነት የክልሉ መንግሥትም እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ ለመመለስ የተዘጋጀ ያለመኾኑን ሁኔታዉ አሳይቷል"ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ በፍጥነት በኢኮኖሚ እያደጉ ካሉ የአፍሪካ አገሮች አንዷ ናት። ሆኖም አንድ ሦስተኛ ዜጎቿ አሁንም ከድህነት ወልል በታች የሚኖሩ ሲኾን በዚህ ዓመት በተከሰተዉ ድርቅ ደግሞ በርካታ ሚሊዮን ሕዝብ ለአደጋ ተጋልጧል።

ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው ድምጽ ያድምጡ፡፡

"ወጣቱ ይህ መንግሥት በሚያደርገው ነገር ሁሉ ተንገሽግሿል"ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:44 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG