ሚኒስትሩ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ የካቲት 5/2015 ዓ.ም ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሳቸውን፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምሽት 5 ሰዓት አካባቢ በማኅበራዊ ድረገጾቹ አስታውቋል፡፡
ብሊንከን እና ልዑካቸው በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ምስጋኑ አረጋ እና ሌሎች የመንግሥት ባለስልጣናት አቀባበል እንደተደረገላቸውም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው በጋራ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ በመረጃው ላይ ቢጠቀስም፣ ስለሚያገኟቸው ባለሥልጣናት ማንነት ግን በይፋ አልተጠቀሰም፡፡
ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝት ያለውን አንደምታ በተመለከተ ለአሜሪካ ድምጽ አስተያየታቸውን የሰጡት የምጣኔ ኃብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ “ጉብኝታቸው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ሻክሮ የቆየው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እየተሸሻለ መሄዱን የሚያመለክት ነው” ብለዋል፡፡
መሰረቱን በአሜሪካ ያደረገው የኢንቨስትመንት ተቋም ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ዓለም አቀፍ ሊቀመንበር የሆኑት የምጣኔ ኃብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻሻል ለሁለቱም ብሔራዊ ጥቅም መረጋገጥ ፋይዳ እንዳለው አመልክተው “በተለይ በጦርነቱ ለደቀቀው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲሁም ለመልሶ ግንባታ ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው” አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ብሊንከን በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የሰብዓዊ መብትሟጋች ድርጅቶች እየጠየቁ ነው፡፡
በአገሪቱ ለተፈጸሙ ሰቆቃዎች ተጠያቂነት የሚኖርበትን ጉዳይ በተመለከተ ዋና የውይይት አጀንዳቸው እንዲያደርጉ የጠየቀው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን የሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች ጥያቄውን ያቀረበው ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ቢሮው በኩል ዛሬ ማለዳ ባወጣው መግለጫ ነው።
“አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ወደ ተሟላ ደረጃ ከመድረሱ በፊት እውነተኛ የሆነ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ብሊንከን ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ግልጽ ማድረግ አለባቸው” ብሏል ሂውማን ራይትስ ዎች በመግለጫው።
ስለ ጉብኝቱ ከሦስት ቀናት በፊት በበይነመረብ ለጋዜጠኞች መግለጫየሰጡት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ፣ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ የማደስ ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፣ ለዚህ ግን “ሀገሪቱን ለብዙ አስርት ዓመታት ወደኋላ የጎተተውን የጎሳ ፖለቲካ ላይ የተመሰረተ የግጭት አዙሪት ለመስበር የሚያስችሉ እርምጃዎችን ከኢትዮጵያ እንፈልጋለን” ብለዋል፡፡