ዋሽንግተን ዲሲ —
ሶማልያ ዋና ከተማ ሞቅዲሾ ውስጥ በሚገኝ አንድ የፖሊስ ጣቢያ አቅራቢያ ዛሬ ረቡዕ በደረሰ የመኪና ውስጥ ቦምብ ፍንዳታ፣ ቢያንስ 3 የፖሊስ መኮንኖች መገደላቸው ተሰማ።
የሞቅዲሾ ፖሊስ ዋና ኮሚሽነር አሊ ሀርሲ ባሬ እንደገለጹት፣ በፍንዳታው ክፉኛ የቆሰለው አሽከርካሪ ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር ውሏልኝ።
ፖሊስ ምርመራ እያካሄደ መሆኑንም ባሬ ጠቅሰዋል።
አል-ሻባብ የውጪ ዜጎች የሆኑ ተዋጊዎችን ከሶማልያ አባረርን ይላሉ
በሌላ በኩል ደግሞ፤ የአል-ሻባብ ነውጠኞች፣ የውጪ ዜጎች የሆኑ ተዋጊዎችን ከሶማልያዋ አውደግሌ ከተማ ዛሬ ረቡዕ ማለዳ አባረናቸዋል ሲሉ አስታወቁ።
አንዳለስ (Andalus) የሚባለው የአል-ሻባብ ራድዮ ይፋ ባደረገው ዘገባ፣ ከሄሊኮፕተር የወረዱትና ወደ ከተማዋ ሊዘልቁ ያቀዱት ልዩ ኃይሎች፣ በአል-ሻባብ ሚሊሽያዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸው ሊመለሱ ተገደዋል ይላል።
ሄሊኮፕተሯ ከማረፏ በፊት ተኩስ ተከፍቶ እንደነበር የገለጹት የአል-ሻባብ ሚሊሻዎች፣ ከመካከላቸው አንድ ሰው መገደሉንም ጨምረው ተናግረዋል።