የኢትዮጵያ መንግሥት በእሥር ላይ የሚገኙትን ጋዜጠኞችን እና ሃሳብን በመግለፅ ነፃነታቸው በመጠቀማቸው ምክንያት የታሠሩትን ሌሎች ሰዎች በሙሉ እንዲፈታ፤ ፀረ-ሽብር አዋጁንም የተቃውሞ ድምፅ ማፈኛ አድርጎ ከመጠቀም እንዲቆጠብ ዩናይትድ ስቴትስ አሳስባለች፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የብሔራዊ ፀጥታ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትናንት ባወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ በቅርቡ በጋዜጠኞች ላይ ዩፈፀመቻቸው እሥራቶች ሃገራቸውን ያሳሰባት መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ታስረው የቆዩ በርካታ የኢንተርኔት አምደኞች ወይም ብሎገሮች መፈታታቸውን ጨምሮ በዚህ ዓመት በታዩ የመሻሻል ምልክቶች ዩናይትድ ስቴትስ ተበረታትታ እንደነበር የጠቆመው የትናንቱ የብሔራዊ ፀጥታ ምክር ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ የፕሬስ መግለጫ “የኢትዮጵያ መንግሥት የመናገር ነፃነት ከበሬታን በማጠናከር እና ዴሞክራሲያዊ እርምጃዎችን በማስፋት ያስመዘገባቸውን ለውጦች እንዲያጠናክር ማሳሰባችንን እንቀጥላለን” ብሏል።
ነፃ ድምፆች መታፈናቸው መቀጠሉ እንዲህ ያሉትን እርምጃዎች፤ እንዲሁም ልማትና የምጣኔ ኃብት ዕድገትን ከማደናቀፍ በስተቀር ሌላ ውጤት አይኖራቸውም ሲሉ አስገንዝበዋል ፕራይስ።
“ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ዕድገት ተምሳሌትና ድምፅ” እያለች ስታደንቃት መቆየቷን ያስታወሱት ኔድ ፕራይስ “ይሁን እንጂ እነዚህ እርምጃዎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው መሠረታቸው ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እና የሰብዓዊ መብቶች መከበር ሊሆን ይገባል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እሥር ላይ የሚገኙትን ጋዜጠኞች እና ሃሳብን በመግለጽ መብታቸው በመጠቀማቸው ምክንያት ብቻ የታሠሩትን ሌሎች ሰዎችንም በሙሉ እንዲፈታ፣ ፀረ ሽብር አዋጁን የተቃውሞ ድምፅ ማፈኛ አድርጎ ከመጠቀም እንዲቆጠብ እና ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችን እና ተቃዋሚዎችን የብዙኃን ስብጥር ሃገር ድምፅነት እንዲያከብር በነፃነት የመፃፍ እና የመናገር መብታቸውን እንዲጠብቅ እንጠይቃለን” ብለዋል የዩናይትድ ስቴትስ የብሔራዊ ደኅንነት መማክርቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ፡፡
የዜና ዘገባውን ከዚህ በታች ካለው የድምፅ ፋይል በመጫን ያድምጡ።