በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሳማንታ ፓወር ባለፈው ቅዳሜ አዲስ አበባ ተገኝተው ከኢትዮጵያየውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር በአካባቢያዊናበኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፤ የሲቪል ማኅበረሰብተጠሪዎችንም አነጋግረዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ ሚሲዮን የፕሬስና የሕዝብ ዲፕሎማሲ ፅ/ቤት ባወጣው መግለጫ እንደጠቆመው አሜሪካዊቱ ዲፕሎማት ሳማንታ ፓወር እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በቡሩንዲ ሁኔታ ላይ ትኩረት ሰጥተው ተነጋግረዋል።
አምባሳደር ፓወር ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በተወያዩበት ወቅት ኢትዮጵያ ባጋጠማት ድርቅና የምግብ ቀውስ በጥልቅ መሥጋታቸውን ተናግረው ኢትዮጵያ ያለባትን ግዙፍ የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ለማሟላት በምታደርገው ጥረት የሃገራቸው ድጋፍ እንደማይለያት በድጋሚ አረጋግጠዋል።
አምባሳደር ሳማንታ ፓወር አክለውም ኦሮምያ ውስጥ የደረሰው የተቃዋሚዎች ሞት ዩናይትድ ስቴትስን እያሳሰባት መሆኑን ለዶ/ር ቴድሮስ የነገሯቸው መሆኑን የሚሲዮኑ የፕሬስ መግለጫ አመልክቷል።
በኦሮሞ ማኅበረሰብ አባላት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ላይም የኢትዮጰይ መንግሥት ለውይይት እንዲቀመጥ ጠይቀዋል።
አምባሣደር ፓወር አክለውም በኢትዮጵያ የነፃና ወገንተኛ ያልሆነ ሲቪል ማኅበረሰብን አስፈላጊነት ጠቁመዋል።
አምባሣደሯ በጉብኝታቸው ወቅት ከሰባት የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ መሪዎች ጋር ተገናኝተው የተነጋገሩ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ሲቪሉ ማኅበረሰብ መንገቀሳቀስ እንዲችልና የዜጎች ተሣትፎም እንዲሰፋ ለማድረግ ጋዜጠኞች፣ የሕግ ባለሙያዎችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሪዎች እያደረጉ ያሉትን “ድፍረት የተመላበት” ያሉትን ጥረት አድንቀዋል።
እነዚህ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ አባላት “ሃገሪቱ ውስጥ ያለውን ፈታኝ የፖለቲካ ሁኔታ ተጋፍጠው” ይበልጥ ግልፅና አሣታፊ የሆነ ኅበረተሰብ እንዲኖር እያሳዩ ላሉት ቁርጠኝነት አመስግነዋቸዋል።
አምባሳደሯ አክለውም ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵየ ውስጥ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ለልማትና ለፀጥታ የምትሰጠውን ድጋፍ እንደምትቀጥልና እነዚህ ሦስት ግቦች ተሣስረው እንዲራመዱ ለማድረግ ያላትን ፅኑ ተገዥነትም አረጋግጠዋል።
ቡሩንዲን አስመልክቶ ሁለቱ ዲፕሎማቶች ባደረጉት ውይይት ሁሉንም ወገኖች አሣታፊ የሆነ የፖለቲካ ንግግሮች ከቡሩንዲ ውጭ የሚጀመሩበትን ሁኔታ መክረዋል። እንዲህ ዓይነቱን ንግግር “ለቡሩንዲ የፖለቲካ መፍትሄ ለማግኘት ብቸኛው ተዓማኒና ዘላቂነት የሚኖረው አማራጭ ነው” ብለውታል።
ሁለቱ ባለሥልጣናት የሶማሊያንና የደቡብ ሱዳንንም የፖለቲካ የሰላም ሁኔታ ያነሱ ሲሆን በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች መካከል የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ እንዲሁን እያደረገች ያለችውን ጥረት ጨምሮ በአካባቢው ፀጥታና መረጋጋት ላይ ኢትዮጵያ እየተጫወተች ያለችውን የመሪነት ሚና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዩናይትድ ስቴትስ አምባሣደር ሳማንታ ፓወር ማድነቃቸውን የሚሲዮኑ የፕሬስ መግለጫ አመልክቷል።
የዘገባውን ዝርዝር ከዚህ ያድምጡ።