በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የተመድ መርማሪ ኮሚሽን የኤርትራ መሪዎች በአለምአቀፍ የወንጀል ችሎት ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርቧል


ፋይል- የተመድ የጀነቫ ጽ/ቤት
ፋይል- የተመድ የጀነቫ ጽ/ቤት

በኤርትራ የሚካሄደውን የሰብአዊ መበት ረገጣ ጉዳይ እንዲመረምር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተሰየመ መርማሪ ኮሚሽን የኤርትራ መንግስትና ወታደራዊ ሃይሏ ይፈጸማሉ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ወንጀሎችን መዝግቧል። የኤርትራ መሪዎች በአለምአቀፍ የወንጀል ችሎትና በሌሎች የፍትህ መድረኮች ቀርበው እንዲዳኙ መርማሪው ኮሚሽን ምክረ-ሃሳብ አቅርቧል።

አጭሩ የኤርትራ ታሪክ በሀይል ተጠቃሚነት የተሞላ ነው። በቀይ ባህር ላይ የምትገኘው የአፍሪቃ ቀንድ ሃገር እአአ በ1993ዓ.ም ነጻ ሀገር ከሆነችበት ጊዜ አንስቶ ከሌሎች ጋር መጋጨት ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥም ከፍተኛ ጭቆና የሚፈጸምባት ሀገር ሆናለች።

ኤርትራ እስካሁን ባለው ጊዜ አንድ ፕረዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂን ብቻ ነው ያየችው።እሳቻውና ሚስጢራዊነት የሰፈነበት ቡድናቸው በመላ የሀገሪቱ የ23 አመታት ታሪክ ስድስት ሚልዮን የሚሆነውን ህዝብ ረግጠው ሲገዙ ኖረዋል።

በአሁኑ ወቅት ታድያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተሰየመ መርማሪ ኮሚሽን ሄግ ያለው አለምአቀፍ የወንጀል ችሎት የኤርትራ ሲቪልና ወታደራዊ አመራርን ለፍርድ እንዲያቀርብ ጥሪ አድርጓል።

የኤርትራን የሰብአዊ መብት አያያዝን የምርመራው ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ማይክ ስሚዝ ስለ ኮሚሽኑ ጥናት ውጤት ያብራራሉ።

ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ማይክ ስሚዝ (ቀኝ)
ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ማይክ ስሚዝ (ቀኝ)

“ያወጣነው ዘገባ ኤርትራ ውስጥ በስብእና ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተደርገው የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ወንጀሎችን መዝግቧል። የባርነት ተግባር እንደሚፈጸም ተረድተናል። ላልተወሰነ ጊዜ እስራት እንዳለ አውቀናል። ግድያ እንዳለ ተገንዝበናል። የማዋከብና የአስገድዶ መድፈር ተግባሮች እንደሚጸሙ፣ ሰዎች በወጡበት እንዲቀሩ የማድረግ ወንጀሎች እንዳሉ ተረድተናል። እነዚህ ሁሉ ከባድ ወንጀሎች ናቸው።”

ኮሚሽኑ ያቀረባቸው ግኝቶች ከአንድ አመት በፊት ካወጣው ሌላ ዘገባ ጋር ይመሳሰላሉ። የኤርትራ መንግስት ዘገባውን አልተቀበለውም። ኮሚሽኑ ተፈጽሙ ስለ ሚባሉት ወንጀሎች እዛ ሄዶ ራሱ እንዲያጣራ ቢጠይቅ የኤርትራ መንግስት አልቀፈቀደለትም። ስለሆነም ኮሚሽኑ ያወጣው ዘገባ በአብዛኛው ከሀገር ከወጡ ኤርትራውያን ስደተኞች ጋር ባደረጋቸው ቃለ-መጠይቆች ላይ የተመሰረተ ነው።

አዲሱ ዘገባ ፕረዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂንም ሆነ ሌሎች ወታደራዊ ባለስልጣኖችን በስም አይጠቅስም። ብራውን ብራይቶን የተባሉ በአትላንቲክ ካውንስል የጥናትና ምርምር ክፍል የሚሰሩ ተንታኝ ታድያ የመርማሪው ኮሚሽን ዘገባ ሰዎችን በስም ባለመጥቀሱ ያቀረበው ምክረ-ሃሳብ ክብደትን ያዳክማል ብለዋል።

“በስብእና ላይ ስለተፈጸሙ ወንጀሎች ከመዘገቡ ክሱ እጅግ ከባድ በመሆኑ የፈጸማቸው ማን እንደሆነ ለመጥቀስ መቻል አለባቸው። ወንጀሉን በመፈጸም ተግባር መጠቀስ ያለባቸው ሰዎች ስም ዝርዝር በዘገባው ውስጥ ተካቶ ለማያት እጠብቃለሁ።”

ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ግን የተለየ አመለካከት አላቸው። ሁማን ራይትስ ዋች የተባለው የሰብአዊ መብት ቡድን ምክትል ስራ አስኪያጅ ለስሊ ሌፍኮው የጦርነት ወንጀል በመፈጸም ተግባር የሚጠረጠሩት ሰዎች ስም ያልተጠቀሰበት ምክንያት አለ ይላሉ።

“ብዙ ምክንያቶች አሉ። አንደኛው ምክንያት ወንጀል የፈጸሙትን ሰዎች አስመልክቶ ያላቸው ማስረጃ ስማቸውን ለመጥቀስ የሚያስችል ያህል ቀጥተኛና ተጨባጭ ባለመሆኑ ሊሆን ይችላል። ሌላው ደግሞ በአሁኑ ወቅት ሰዎቹን በስም በመጥቀስ ማስጠንቀቅያ ሊሰጥዋቸው ስላልፈልጉ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ባህሪያቸውን እንዲለውጡ ሊያደርጋቸው ይችላልና።”

ሌዝሊ ሌፍኮ አያያዘውም በስም የሚጠቀሱት ሰዎች አስቀድመው ካወቁ ወደ ሌላ ሃገር የመጥፋት እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ ብለዋል። ለምሳሌ የቻድ ፕረዚዳንት ሂሰን ሀብሬ እአአ በ 1990 ዓ.ም ከስልጣን ከተገለበጡ በኋላ ወደ ሴኔጋል ሸሹ ሲሉ ሊዝሊ ሊፍኮ አስገንዝበዋል።

ሁማን ራይትስ ዋች ምክትል ስራ አስኪያጅ ለስሊ ሌፍኮው
ሁማን ራይትስ ዋች ምክትል ስራ አስኪያጅ ለስሊ ሌፍኮው

የኤርትራ ጉዳይ ደግሞ ሌሎች የተወሳሰቡ ነገሮች አሉበት። ኤርትራ ነጻ ሀገር ከሆነች ብዙም ሳይቆይ ከኢትዮጵያ ጋር ግጭት ውስጥ ገብታለች። እአአ ከ 1998 እስከ 2000 ዓ.ም በነበረው ጊዜ ውስጥ የድንበር ውጊያ አካሄደዋል። በውጊያውም በ 80,000 የሚገመቱ ሰዎች አልቀዋል። አሁንም ቢሆን በየጊዜው አነስተኛ የተኩስ ልውውጦች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

የሁማን ራይትስ ዋች ምክትል ስራ አስኪያጅ ለስሊ ሌፍኮው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የጦርነት ሁኔታን የማብቃቱ ጉዳይ በኤርትራ ያለውን የሰብአዊ መብት መሻሽእል ድረስ ርቆ መሄድ ያለበት ጉዳይ ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ጠባቸውን መፍታት አለባቸው ይላሉ ሌፍኮ። ሁለቱም ወገኖች ድንበራቸውን ለይቶ ለማስመር የተደረገው ጥረት ውጤቶችን መቀበል አለባቸው። ሌላው አስፈላጊ ነገር ደግሞ በአፍሪቃ ቀንድ አገሮች የሚካሄዱ ግጭቶችና የፖለቲካ ንትርክች መፍትሄ እንዲያገኙ የሚያስችል ክልላዊ ጥረት እንዲኖር ሌዝሊ ሌፍኮ አስገንዝበዋል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።

የተመድ መርማሪ ኮሚሽን የኤርትራ መሪዎች በአለምአቀፍ የወንጀል ችሎት ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርቧል
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:26 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG