በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዐማራ ክልል ግጭት መቀጠሉን ተከትሎ በመጪው ወር ሊደረግ የነበረው የጣና ፎረም ስብሰባ ተላለፈ


ፎቶ ፋይል፦ ባህር ዳር ከተማ እአአ ኅዳር 06/2020
ፎቶ ፋይል፦ ባህር ዳር ከተማ እአአ ኅዳር 06/2020

በኢትዮጵያ ዐማራ ክልል የሰው ህይወት የቀጠፈው ግጭት መቀጠሉን ተከትሎ፣ በአፍሪካ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር የተቋቋማው ጣና ሮረም በመጪው ጥቅምት ሊያደርገው የነበረውን ስብሰባ ወደ ሚያዚያ አስተላልፏል።

መድረኩ ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ ስብሰባው የተላለፈው “ባልተጠበቁ ሁኔታዎች” ምክንያት ነው ብሏል። ጣና ፎረም በየዓመቱ በዐማራ ክልል ይደረግ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን የፌዴራል መንግሥት በክልሉ ያሉ ኃይሎችን ትጥቅ ለማስፈታት በሚያደርገው ጥረት አካባቢው የግጭት አውድማ ሆኗል ሲል አሶስዬትድ ፕረስ በዘገባው አመልክቷል።

ጣና ፎረም የተባለው ስብስብ “ለአህጉሪቱ አሳሳቢ ችግሮች አፍሪካ-መር መፍትሄ” ለመሻት እንደሚጥር ይናገራል። “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በማዕከል ሥልጣንን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ጥረት የሚገዳደሩ አንዳንድ ብሔሮች በመኖራቸው፣ አሳሳቢ የተባሉት አንዳንዶቹ ችግሮች በፎረሙ ጓሮ እየተከሰቱ ናቸው” ሲል ዘገባው አክሏል።

ላሊበላን ጨምሮ በክልሉ ባሉ ከተሞች ሕይወት የቀጠፉ የድሮን ጥቃቶች እና የከባድ መሣሪያ ድብደባዎች መካሄዳቸውን፣ ፎረሙ በሚካሄድባት ባህር ዳር ከተማም ጦርነት መካሄዱን፣ ከሰማይ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን እንዲሁም በጎዳናዎች ላይ ተኩስ እንደሚሰሙ ነዋሪዎች መናገራቸውን የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጣና ፎረም አጋሮች መሆናቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፣ ከፎረሙ አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ ጠቁሟል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG