በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዐማራ ክልል ግጭት ቢያንስ 183 ሰዎች እንደ ሞቱ ተመድ አስታወቀ


ማርታ ሁርታዶ - የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ቢሮ ቃል አቀባይ
ማርታ ሁርታዶ - የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ቢሮ ቃል አቀባይ

በዐማራ ክልል፣ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ በተስፋፋው ግጭት፣ በትንሹ የ183 ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የመብቶች ጥሰት ተመራማሪዎቹን ጠቅሶ አስታውቋል። ግድያ፣ ጥቃት እና የመብቶች ጥሰት እንዲቆምም ጠይቋል።

በዐማራ ክልል፣ ከሐምሌ ወር ጀምሮ በተቀሰቀሰው እና በበርካታ አካባቢዎች በተስፋፋው ግጭት፣ በትንሹ የ183 ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የመብቶች ጥሰት ተመራማሪዎቹን ጠቅሶ ሲያስታውቅ፤ ግድያ፣ ጥቃት እና የመብቶች ጥሰት እንዲቆምም ጠይቋል።

በክልሉ፣ በዓመቱ ውስጥ ውጥረቱ እየተባባሰ የመጣው፣ መነሻውን በአጎራባቹ የትግራይ ክልል አድርጎ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የተካሔደውና የዐማራ ክልል ልዩ ኀይሎች፣ ሚሊሻዎች እና የፋኖ ታጣቂዎች የተሳተፉበት አውዳሚ ጦርነት ከአበቃ በኋላ ነው።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ቢሮ ቃል አቀባይ ማርታ ሁርታዶ፣ ጄኔቫ ለሚገኙት ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በክልሉ እያሽቆለቆለ ያለው የሰብአዊ መብቶች ይዞታ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል።

አክለውም፤ “በኢትዮጵያ አንዳንድ ክልሎች እያሽቆለቆለ ያለው የሰብአዊ መብቶች ኹኔታ፣ እጅግ በጣም አሳስቦናል። በዐማራ ክልል፣ በኢትዮጵያ ጦር እና በክልሉ የፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተቀሰቀሰውና ሐምሌ 28 ቀን የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ተከትሎ፣ ኹኔታው በጣም ተባብሷል። መሥሪያ ቤታችን መሰብሰብ በቻለው መረጃ መሠረት፣ ግጭቱ፥ በሐምሌ ወር ላይ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንሥቶ፣ ቢያንስ 183 ሰዎች ተገድለዋል።” ብለዋል።

የፌዴራል መንግሥት፣ በመላው አገሪቱ የሚገኙ የክልል ልዩ ኀይሎችን አፍርሶ ወደ ጸጥታ ተቋማት ዳግም እንደሚያደራጅ ያስታወቀው፣ በሚያዝያ ወር ነበር። ኾኖም፣ ርምጃው፣ የክልላችንን የጸጥታ ዐቅም ያዳክማል፤ በሚሉ የዐማራ ብሔርተኞች ተቃውሞ አሥነስቷል።

ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ፣ በብሔራዊ ጦር ሠራዊቱ እና በክልሉ በሚገኙ የፋኖ ተዋጊዎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ፣ የዐዲስ አበባ ባለሥልጣናት፣ ሐምሌ 28 ቀን፣ እስከ ስድስት ወራት ሊቆይ የሚችል የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዐውጀዋል።

ዐዋጁ፣ ለባለሥልጣናት፣ ተጠርጣሪዎችን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለመያዝ፣ የሰዓት እላፊ ገደብ ለመጣልና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ለመከልከል፣ ሰፊ ሥልጣን እንደሰጣቸው፣ የሰብአዊ መብቶች ቢሮው ቃል አቀባይ ሁርታዶ ገልጸዋል።

ሁርታዶ፣ በአስቸኳይ ዐዋጁ ሥር፣ ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች እንደታሰሩ የሚያሳዩ መረጃዎች እንደደረሳቸው አመልክተው፣ “ከታሰሩት ውስጥ አብዛኞቹ፣ የፋኖ ደጋፊዎች ናቸው፤ ተብለው የተጠረጠሩ ወጣቶች ናቸው፤” ሲሉ አብራርተዋል።

ቃል አቀባይዋ አክለውም፣ “ከነሐሴ ወር መጀመሪያ አንሥቶ፣ በጅምላ የቤት ለቤት ፍተሻ እየተካሔደ ነው። በመኾኑም ባለሥልጣናቱ፥ የጅምላ እስራትን እንዲያቆሙ፣ ማንኛውም ነፃነትን የመንፈግ ተግባር፣ በፍርድ ቤት እንዲታይና በዘፈቀደ የታሰሩት እንዲፈቱ እንጠይቃለን፤" ሲሉ ጥሪአቸውን አቅርበዋል።

የግጭቱ ተሳታፊዎችም፥ ግድያን፣ የመብቶች ጥሰቶችንና ጥቃቶችን እንዲያቆሙም ጠይቀዋል።

በሌላ ዜና፣ በደብረ ታቦር ከተማ፣ በመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በነበረው ግጭት፣ ሦስት ንጹሐን ዜጎች እንደተገደሉና 31 ሰዎች እንደቆሰሉ፣ የሆስፒታል ምንጮች አረጋገጠዋል።

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ግን፣ የሞቱት ንጹሐን ዜጎች ቁጥር፣ ከተጠቀሰው እንደሚልቅና ሥርዐተ ቀብራቸውም፣ በዛሬው ዕለት በየአብያተ ክርስቲያናቱ እንደተፈጸመ ተናግረዋል።

ዳግም ግጭት አገርሽቶባቸው በነበሩት የዐማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞች ማለትም የደብረ ታቦር፣ የደብረ ማርቆስ እና የፍኖተ ሰላም ከተሞች፣ ዛሬ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴአቸው እንደተመለሱ፣ ነዋሪዎቹ አክለው ገልጸዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG