በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዐማራ ክልል “የልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት” ተቃውሞ ግጭቶች ተባብሰው ቀጥለዋል


ትላንት ሚያዚያ 3/2015 ዓ.ም በኮምቦልቻ ከተማ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ
ትላንት ሚያዚያ 3/2015 ዓ.ም በኮምቦልቻ ከተማ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ

የኢትዮጵያ መንግሥትን፣ የክልሎች ልዩ ኃይሎች መዋቅራዊ ለውጥ ውሳኔ በመቃወም፣ በአማራ ክልል ተጠናክሮ በቀጠለው የስድስተኛ ቀን ተቃውሞ፣ በርካታ ሰዎች በጥይት መመታታቸውን፣ የአካባቢውን ባለሥልጣናት እና አንድ የሆስፒታል ሠራተኛን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።

ከኢትዮጵያ ዐሥራ አንድ ፌዴራላዊ ክልሎች፣ በመጠኑ ኹለተኛ በኾነው የዐማራ ክልል የተነሣው ተቃውሞ፣ የመንግሥት ዕቅድ፥ ሕዝቡንና አስተዳደራዊ ወሰኑን ከሌሎች ክልሎች ለሚሰነዘር ጥቃት ተጋላጭ ያደርገዋል፤ በሚል ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በፌዴራሉ መንግሥት እና በህወሓት ኃይሎች መሀከል፣ ለኹለት ዓመታት የተካሔደውን አስከፊ ጦርነት፣ በኅዳር ወር በፕሪቶሪያ በተፈረመ የሰላም ስምምነት ለአስቆመው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት፣ ሰሞኑን በዐማራ ክልል እየተባባሰ የቀጠለው አለመረጋጋት፣ ዐዲስ የጸጥታ ችግር ፈጥሮበታል።

ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ፣ በዐማራ ክልል ልዩ ልዩ ከተሞች ሕዝባዊ ተቃውሞ መቀስቀሱን የገለጹት የአካባቢው ተወላጆች፣ በኮምቦልቻ የተካሔደው ተቃውሞ ወደ ግጭት መቀየሩን የሮይተስ ዘገባ አመልክቷል።

ሮይተርስ ያነጋገራቸው የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ መሐመድ አሚን፣ ግጭቱ የተቀሰቀሰው፥ የፌደራል መንግሥት መከላከያ ሠራዊት፣ አንዳንድ የዐማራ ክልል ኃይሎችን አፍነው መውሰዳቸውን የሚገልጽ የሐሰት መረጃ መሠራጨቱን ተከትሎ እንደኾነ ጠቅሰው፣ ይህን የተቃወሙ ነዋሪዎች፣ የጦር ካምፑ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን አስረድተዋል።

“በድንጋይ እና በጥይት ቆስለው ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ነበሩ። ከእኒኽም፣ የከተማው የጸጥታ አካላት(የፌደራል ጦር ሠራዊት) እና ተቃዋሚዎች እንደሚገኙበት ያመለከቱት የከተማው ከንቲባ፣ የተጎጂዎችን ቁጥር በሌላ ጊዜ እንደሚያስታውቁ ተናግረዋል።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ፣ የፌዴራል ወታደሮች፣ የክልሉን ልዩ ኃይል አባላት እና ሌሎች ታጣቂዎች ለማሰር ሞክረው እንደነበረና ይህም ነዋሪዎች ጣልቃ እንዲገቡ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል። የዐይን እማኙ አክለውም፣ በጥይት የተገደሉ የአምስት ሰዎችን አስከሬንና የቆሰሉ 10 ሰዎች ማየታቸውን ተናግረዋል።

በኮምቦልቻ አቅራቢያ በምትገኘው ደሴ ከተማ የሚገኙ አንድ የሕክምና ባለሞያ፣ ከኮምቦልቻ ቆስለው የመጡ 12 ግለሰቦች ወደሚሠሩበት ሆስፒታል መግባታቸውንና ሰዎች ስለ መገደላቸውም መስማታቸው አመልክተዋል። የሟቾቹን ቁጥር ከገለልተኛ አካል ማጣራት አለመቻሉን የጠቀሰው ሮይተርስ፣ የዐማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር፣ የፌዴራል መንግሥት እና የመከላከያ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይም፣ ስለ ጉዳዩ ምላሽ እንዳልሰጡት ገልጿል፡፡

በኮምቦልቻ የመከላከያ ሠራዊቱ ካምፕ ላይ ግጭቱ የተከሠተው፣ በክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር በሚገኝ አንድ የምግብ እና መጠጥ ቤት ውስጥ፣ ፖሊስ ሁለት ያለውና የሕክምና ባለሞያዎች ደግሞ ሦስት ያሉት ሰዎችን ሕይወት ያጠፋና ዐሥር ሰዎችን ያቆሰለ የቦምብ ፍንዳታ ከደረሰ ከአንድ ቀን በኃላ ነው። ፍንዳታው በማን እንደተፈጸመም ይኹን ከተቃውሞ እንቅስቃሴው ያለውን ግንኙነት በተመለከተ እስከ አሁን በውል የታወቀ ነገር የለም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በዐማራ ክልል ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት፣ በሚሊየኖች ለሚቆጠሩ የሰብአዊ ረድኤት ጠባቂዎች ያደርስ የነበረውን የምግብ ርዳታ፣ ለጊዜው ማቆሙን ትላንት ማክሰኞ አስታውቋል።

ኹለት የካቶሊክ ተራድኦ ሠራተኞች፣ ባለፈው እሑድ በዐማራ ክልል ቆቦ ከተማ አቅራቢያ መገደላቸውን የርዳታ ድርጅቱ የገለጸ ሲኾን፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርም፣ በዚያው ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ አንዲት አዋላጅ ነርስ እና የአምቡላንስ አሽከርካሪ፣ በታጣቂዎች ጥይት ተመትተው መቁሰላቸውን፣ ትላንት ማክሰኞ አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG