የሱዳን ፕሬዚደንት ኦመር አል በሺር በኒው ዮርክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ መገኘት እንዲችሉ የኦባማ እስተዳደር ቪዛ ይሰጣቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ሲል ተናገረ።
ፕሬዚደንት በሺር በመስከረም ወር በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዲገኙ በድርጅቱ ዋና ጸሓፊ ባን ኪ ሙን ተጋብዘዋል ያሉት የሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር አህመድ ቢላል ዩናይትድ ስቴትስ ጉባዔው የሚስተናገድባት እንደመሆንዋ የመግቢያ ፈቃድ የመስጠት ግዴታ አለባት ብለዋል።
"በርግጥም ካሁን በፊት ቪዛ እንዲሰጣቸው አመልክተው ተከልክለዋል። አሁን ግን በዋና ጸሓፊው ስለተጋበዙ ዩናይትድ ስቴትስም የዓለም አቀፉ ድርጅት መቀመጫ እንደመሆንዋ ልንከለከል አይገባም፣ ከሰጧቸው ጉባዔው ላይ ይገኛሉ" ሲሉ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አክለዋል።
ፕሬዚደንት ኦመር አል በሺር ባለፈው ሳምንት በካምፓላ የዩጋንዳ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ የአምስተኛ የስልጣን ዘመን ቃለ ማሃላ ስነ ስርዓት ላይ መገኘታቸውና የዩጋንዳው ፕሬዚደንት የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤቱን "ይሄን የዕርባና ቢሶች ጥርቅም አልደግፈውም" ብለው ሲዘልፉ የዩናይትድስ ስቴትስ ልዑካን በተቃውሞ ስነ ስርዓቱን ረግጠው መውጣታቸው ይታወሳል።