በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሶማልያንና የኤርትራን ጉዳይ የሚከታተለው ተቆጣጣሪ ቡድን ሶማልያን በምታሳየው ትብብር ሲያሞግስ ኤርትራን ግን ነቀፈ


የቬንዝዊውላ አምባሳደር የሆኑት ራፋኤል ዳርዮ ራሚሪዝ ካሬኖ
የቬንዝዊውላ አምባሳደር የሆኑት ራፋኤል ዳርዮ ራሚሪዝ ካሬኖ

የተበበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት የወሩ ተረኛ ሊቀ-መንበርና ሶማልያንና ኤርትራን በሚመለከት የማዕቀብ ኮሚቴ ሊቀመንበር ራፋኤል ዳርዮ ራሚሪዝ ካሬኖ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተሰየመው ተቆጣጣሪ ቡድን ሶማልያንና ኤርትራን በሚመልከት ያቀረውን ዘገባ ባለፈው ሀሙስ ለጸጥታው ምክር ቤት አባላት አሰምተዋል። የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ ምላሽ ሰጥቷል።

የቬንዝዊውላ አምባሳደር የሆኑት ራፋኤል ዳርዮ ራሚሪዝ ካሬኖ ስለማዕቀቡ ኮሜቴ ስራዎች ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ባቀረቡት ዘገባ ኮሚቴው የሶማልያንና የኤርትራን ጉዳይ የሚመለከተው ተቆጣጣሪ ቡድን ያቀረበውን የመጨረሻ ዘገባ ተመልክቶ ስላቀረባቸው ምክረ ሃሳቦች እንደተወያየ ገልጸዋል።

ተቆጣጣሪው ቡድን ባቀረበው ዘገባ መሰረት እምቁ የሶማልያ የባህርና የተፈጥሮ ሃብት አለም አቀፍ ትኩረት እየሳበ ቢሆንም በአስተዳደር ጉድለት ምክንያት ተግባራዊ ሊሆን እንዳልቻለ ይህም ለሃገሪቱ ደህንነት፣ ሰላምና መረጋጋት አደጋ ሊሆን እንደሚችል ማስገንዘቡን አምባሳደር ራሚሬዝ ጠቁመዋል።

“የሶማልያ የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍን በሚመለከት በሶማልያው ፌደራላዊ መንግስትና በክልላዊ አስተዳደሮች መካከል ላለው ውጥረት ምክንያት የሆነው ማዕከላዊው መንግስትና ክልላዊ አስተዳደሮች በየበኩላቸው ከዓለም አቀፍ የነዳጅ ዘይትና የጋዝ ኩባንይዎች ጋር ውል ስለሚፈራረሙ እንደሆነ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተሰየመው ተቆጣጥሪ ቡድን ገልጿል።”ብለዋል አምባሳደር ራሚሬዝ።

አል-ሸባብ በሀገሪቱና በአከባቢው ስለሚደቅነው አደጋ ተቆጣጣሪው ቡድን ሲያስረዳ ጽንፈኛው ቡድን ጉዳት ቢደርስበትም በአደጋነት እንደቀጠለ ጠቅሷል።

“አል-ሸባብ በሶማልያ ያለው የአፍሪቃ ህብረት የሰላም ጥበቃ ተልእኮና የሶማልያው ብሄራዊ ሰራዊት ከሚገባው በላይ በሰፊ አከባቢዎች የተሰራጩ መሆናቸው ራሱ አመቺ ሆኖለታል። ስለሆነም የተሰራጩባቸው ወታደራዊ ሰፈሮች ለአል-ሸባብ ጥቃት እንደሚጋለጡ ተቆጣጣሪው ቡድን አስረድቷል። ቡድኑ በተጨማሪም አል-ሸባብ ከየመንና ከአል-ቃዒዳ ከአረብ ባህረ-ገብ መሬት ጋር ያለውን ግንኑነት ክፍት ለማድረግ ይሞክር እንደነበር ለመገንዘብ ችሏል።”

የሶማልያ ፌደራል መንግስትና ክልለዊ አስተዳደሮች ከአል ሸባብ ነጻ የውጡትን ግዛቶች ለመቆጣተር አለመቻላቸው ራሱ በማህበረሰቦች መካከል ውጥረት እንዲሰፍንና ግጭት እንዲፈጠር ማድረጉን ቡድኑ በዘገባው መግለጹን አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

የሶማልያ መንግስት ከውጭ ያስገባቸውን መሳርያዎች ለተቆጣጣሪው ቡዳን በጊዜው በማሳወቁና በአቀራረቡ ጥራት ተቆጣጣሪው ቡድን አሞግሶታል። ይሁንና የጸጥታ ሃይሎች የሚገኙባቸውን ቦታዎችና አወቃቀራቸውን በሚመለከት ተጨባጭ መረጃ አለማግኘቱ እንዳሳሰበው መግለጹን የአምባሳደሩ ዘገባ ጠቅሷል።

ተቆጣጣሪው ቡድን ኤርትራ አል-ሸባብን የምትደግፍ መሆንዋን የሚያሳይ ማስረጃ እንዳላገኘ አምባሳደር ራሚሬዝ ባቀርቡት ዘገባ ጠቅሰዋል።

“ቡድኑ የኤርትራ መንግስት ዐል ሸባብን እንደሚደግፍ የሚያሳይ ማስረጃ አላገኘም። ይሁንና ኤርትራ የኢትዮጵያ የታጠቁ ቡድኖችን እንደምትደግፍ ተቆጣጣሪው ቡድን በዘገባው ጠቅሷል። ይህም የ 1907 ውሳኔ ምዕራፍ 16 ን ይጻረራል። ቡድኑ ከኤርትራ መንግስት ጋር በተለየየ ጊዜ የተነጋገረ ቢሆንም የመተባበር ፍላጎት አላሳየም ብሏል በዘገባው። በጅቡቲና በኤርትራ መካከል ያለውን የድንበር ጠብ በመፍታት ረገድም መሻሻል እንዳልታየ ቡድኑ ገልጿል። ኮሚቴው ቀጠር የምታካሄደው ሽምግልና ለጉዳዩ መፍትሄ አስተዋጾ ያደርጋል የሚል ተስፋ አለው።”

ቡድኑ በተጫማሪም የኤርትራ ወታደሮች የመን ውስጥ ከአረብ ሀገሮች ጥምረት ጋር ሆነው ይዋጋሉ የሚል ያልተረጋገጠ ወሬ በዘገባው መጥቀሱን አምባሳደር ራሚሬዝ ባቀረቡት ዘገባ ጠቅሰዋል።

"የኤርትራ ወታደሮች የመን ውስጥ ከአረብ ሀገሮች ጥምረት ጋር ሆነው እንደሚዋጉ የሚገልጽ ያልተረጋገጠ ወሬ ቡድኑ በዘገባው ጠቅሷል። ይህ ከተረጋገጠ የኤርትራውያኑ ተሳትፎ የውሳኔው ምዕራፍ ስድስትን መጣስ ይሆናል።”ብለዋል።

የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት በቀረብው ዘገባ ላይ መግለጫ አውጥቷል።

“ተቆጣጣሪው ቡድን ዘግይቶም ቢሆን የኤርትራ መንግስት አል-ሸባብን የሚደግፍ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳላገኘ መግለጹን ኤርትራ በበጎ ትቀበለዋለች። ይህ ሀቅ ራሱ በኤርትራ ላይ ፍትህ በጎደለው መልክ ላለፉት ሰባት አመታት ያህል የተጣለውን ማዕቀብ ለማንሳት በቂ መሆን አለበት።

ተቆጣጣሪው ቡድን የኤርትራ ወታደሮች የመን ውስጥ ከአረብ የጥምረት ሀገሮች ጋር ሆነው ይዋጋሉ የሚል ያልተረጋገጠ ወሬ እንደደረሰው በዘገባው መጥቀሱን በሚመለከት ደግሞ ከእውነት የራቀ ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ያወጣው መግለጫ አስተባብሏል።

“ኤርትራ በፊትም ቢሆን ፍትህ የጎደለው የማዕቀብ ውሳኔ የተላለፈው ኤርትራን ለማዋከብ የታቀደ የፖለቲካ አላማ ያለው እንዲሁም ኢትዮጵያ የአለም አቀፍ ህግን በመጣስ ባድመን ጨምሮ የኤርትራ ግዛት የመያዝዋን አቅጣጫ ለማስቀየር ነው ስትል ቆይታለች” ይላል የኤርትራው መግለጫ።

ራፋኤል ዳርዮ ራሚሪዝ ካሬኖ የቡዱኑን ዘገባ ካሰሙ በኋላ አስተያየታቸውን ከስጡት አባላት መካከል ጥቂቶቹን ለመግለጽ ያህል የብሪታንያ ተወካይ የሆኑት አምባሳደር በሶማልያ መንግስትና በተቆጣጣሪው ቡድን መካከል ግልጽና ገንቢ የሆነ ግንኙነት እንዲኖር አሳስበዋል።

የኤርትራ ካርታ
የኤርትራ ካርታ

“በሶማልያ መንግስትና በተቆጣሪው ቡድን መካከል ግልጽና ገንቢ የሆነ ግንኙነት እንዲኖር ሊሰመርበት ይገባል። ይህ ጉዳይ ከቅርብ አመታት ወዲህ ተሻሽሏል። የምርጫው ጊዜ እየተቃረበ በመሆኑ የፐለቲካው ሙቀት መጨመሩ አይቀርም። ስለሆነም ሁለቱም ወገኖች ባይስማሙም እንኳን ግንኙነታቸው ገንቢ ሆኖ መቀጠል ይኖርበታል።”

ኤርትራ ከተቆጣጣሪው ቡድን ጋር ያላት ግንኑነት ግን ወደ ገንቢነትም አይጠጋም ብለዋል።

“የሚያሳዝነው ኤርትራ ከተቆጣጣሪው ቡድን ጋር ያላት ግንኑነት ግን ወደ ገንቢነትም አይጠጋም። በመሰረቱ ተቀባይነት ሊኖረው በማይችልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው። ቡድኑ ይህ ምክር ቤት የሰጠው የምዕራፍ ሰባት ውክልና ያለው በመሆኑ በቀላሉ ሊታይ የሚችልና ችላ ሊባል የሚገባው አይደለም። ስለሆነም ኤርትራ ከቡድኑ ጋር መተባበር ይኖርባታል። ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡም መፍቀድ አለባት። ይህ ላለፉት ሶስት አመታተ አለመደረጉ ያስቆጣል። ኤርትራ ይህን በማድረግ የጸጥታው ምክር ቤት ስለማዕቀቡ ጉዳይ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ክርክር እንዲያደርግ ማስቻል አልያም መገለልን መምረጥ ይኖርባታል።”

በጸጥታው ምክር ቤት የዩናትድ ስቴትስ ተወካይ የሆኑት አምባሳደር ደግሞ ሶማልያ በግልጽነትና በፍትሀዊ አሰራር ላይ የተመሰረተና ተጠያቂነት ያለው መንግስት እንዲኖራት ይህ የጸጥታ ምክር ቤት አጥብቆ ለመርዳት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

“ሶማልያ በግልጽነትና በፍትሀዊ አሰራር ላይ የተመሰረተና ተጠያቂነት ያለው መንግስት እንዲሁም የሀገሪቱ የተፈጥሮ ሃብት ለህዝቡ በሚጠቅም መንገድ እንጂ በሌቦች እንዳይዘረፍ የማድረግ ብቃት ያለው መንግስት እንዲኖራት ይህ የጸጥታ ምክር ትኩረት ሰጥቶ በትጋት መርዳት እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው።ኤርትራን በሚመለከት ደግሞ ኤርትራ ማእቀቡ እንዲነሳላት የምታደርገው ጥሪ ከቁም ነገር እንዲቆጠር ከተፈልገ የሀገሪቱ መንግስት ከተቆጣጣሪው ቡድንና ከማዕቀቡ ኮሚሽን ጋር ገንቢ ግንኙነት ለማደረግ አሻፈረኝ ማለቱን መለወጥ አለበት። ተቆጣጣሪው ቡድን ተልእኮውን እንዳይፈጽም ማሰናከልና ኤርትራ የተጣለባትን መዕቀብ አታከብርም ከሚለው ወሬ ጋር ተጣምሮ የኤርትራ ባለስልጣኖች ማዕቀቡ እንዲነሳ የሚያሰሙትን ፍላጎት የሚጻረር ነው። ስለሆነም ኤርትራ ተቆጣጣሪው ቡድን ወደ ሀገሪቱ ገብቶ ስራውን እንዲያካሄድ እንድትፈቅድ ጥሪ እናደርጋለን።”

ኤርትራና ኢትዮጵያ
ኤርትራና ኢትዮጵያ

በጸጥታው ምክር ቤት የሩስያ ፌደረሽን ተወካይ ደግሞ፣“በሶማልየ ላይ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ በከፊል መነሳት በሀገሪቱ ወታደራዊ ሃይል ምን ያህል ውጤት እንዳስገኘ አይተናል። ኤርትራን በሚመልከት ያለው ገደብ ግን ፍጹም የተለየ ነው። ተቆጣጣሪው ቡድን የኤርትራ መንግስት አል-ሸባብን የሚደግፍ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳላገኘ ማወቃችን አስደስቶናል። ሀገሪቱ መረጋጋት እንዳይኖር ስለምታ አካሄደው ተግባርም አሳማኝ ማስረጃ አላየንም። ስለሆነም ተቆጣታሪው ቡድን በዘገባው ላይ በማስረጃ የተረጋገጠ ኢንፎርሜሽን ብቻ እንዲያሰፍር ጥሪ እናደርጋለን።”

በመጨረሻም ራፋኤል ዳርዮ ራሚሪዝ ካሬኖ በሶማልያና ኤርትራ የማዕቀብ ኮሚቴ ሊቀመንበርነታቸው መሰረት ኤርትራን እንዲጎበኙ ከኤርትራው ፕረዚዳንት የግብዣ ደብዳቤ እንደተቀባሉ ገልጸዋል።

ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG