በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፕሬዝዳንት ሳል በሚያዝያ ወር ስልጣን እለቃለሁ አሉ


የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል
የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል

የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል በመጭው የሚያዝያ ወር ስልጣናቸውን እንደሚለቁ በትናንትናው ዕለት ቢያስታውቁም፤ ቀደም ሲል የፊታችን እሁድ ሊካሄድ ታቅዶ ለሌላ ጊዜ የተላለፈው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚካሄድበትን አዲስ ቀን ግን ይፋ አላደረጉም።

የሁለተኛ ዙር የስልጣን ዘመናቸውን በማጠናቀቅ ላይ ያሉት ሳል የተፎካካሪዎችን ማንነት አስመልክቶ በተቀሰቅሰው እና አሁንም ድረስ እልባት ባላገኘው ውዝግብ ሳቢያ ምርጫውን ለ10 ወራት ማራዘማቸው ይታወሳል። ይሁንና ሳል ስልጣኔን እለቃለሁ ካሉበት የሚያዝያ ወር አስቀድሞ አዲስ ፕሬዝዳንት መመረጥ ስለመቻል አለመቻሉ ግን ግልጽ አይደለም። ፕሬዝዳንቱ የወሰዱትን የቀደመ እርምጃቸውን ‘ሕገ-ወጥ ነው’ ሲል ውድቅ ያደረገው የሃገሪቱ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት በበኩሉ፡ መንግሥት በተቻለ ፍጥነት አዲስ የምርጫ ቀን እንዲያዘጋጅ ትእዛዝ ሰጥቷል።

“ሀገር ያለ ፕሬዚዳንት መቀጠል እንደማትችል ግልጽ ነው” ያሉት ሳል፡ “ውይይት ቀጣዩን ይወስናል። እናም ከአንዳች መግባባት ላይ እንደሚያደርሰን ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል። በመጭው ሳምንት ከፖለቲካ መሪዎች ጋር እንደሚወያዩም ተናግረዋል። ሴኔጋል በምእራብ አፍሪካ በጣም የተረጋጋ ዲሞክራሲ ካላቸው ሀገራት አንዷ ተደርጋ ትታያለች። ይሁን እንጂ በምርጫ ጉዳይ ዙሪያ የተነሱ አለመግባባቶች ሀገሪቱን የሰው ሕይወት ጭምር ከጠፋበት የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ማስገባታቸው ይታወቃል። በሰላማዊ ሰልፎቹ ወቅት ሦስት ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ሲገደሉ ሌሎች በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውም ተዘግቧል።

የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ሰላማዊ ሰልፎችን ለማካሄድ ያቀዱ ተቃዋሚ ወገኖች፡ ምርጫው በፍጥነት ይካሄድ ዘንድ በሳል ላይ ግፊት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG