በሴኔጋል፤ መንግስት በዚህ ወር መደረግ የነበረበትን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለማራዛም የወሰነውን ውሳኔ፣ የአገሪቱ የህገ መንግስት ምክር ቤት ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ፣ ፕሬዝደንት ማኪ ሳል “በተቻለ ፍጥነት” ምርጫ እንደሚደረግ ዛሬ ዓርብ አስታውቀዋል።
“የሪፐብሊኩ ፕሬዝደንት የህገ መንግስት ምክር ቤቱን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር አቅደዋል” ሲል የፕሬዝደንቱ ጽ/ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ፕሬዝደንት ማኪ ሳል በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረውን ምርጫ ወደ ታህሳስ ማስተላለፋቸው፣ በሴኔጋል የሰው ሕይወትን የቀጥፈ ተቃውሞ እንዲካሄድ አድርጓል። በመፈንቅለ መንግስት በሚታመሰው ቀጠና የሰላም እና መርጋጋት ተምሳሌት ተደርጋ የምትታየውን አገር ቀውስ ውስጥ ከቷታል።
ምርጫው በመቃረብ ላይ ባለበት ወቅት፣ መንግስት እንዲተላለፍ የወሰነውን ውሳኔ ፓርላማውም አጽድቆት እንደነበር ሲታወቅ፣ ምርጫው እንዳይተላለፍ ሲቃወሙ የነበሩ የፓርላማ ዓባላትን የፀጥታ ኃይሎች ካሰወጡ በኋላ ወደ ማጽደቅ እንደተገባም የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።
የፓርላማው ውሳኔ፣ በመጪው ሚያዚያ የስልጣን ዘመናቸው የሚያከትመውን ሳል፣ አዲስ ተተኪ ፕሬዝደንት እስኪሰየም በስልጣን ላይ እንዲቆዩ የሚያስችል ነበር ተብሏል።
ባለፉት ቀናት በተደረጉ ተቃውሞዎች ሶስት ሰዎች እንደተገደሉ ሲዘገብ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማኅበረሰቡ፣ ዛሬ እና ነገ ቅዳሜ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲደረግ ጥሪ አድርገዋል።
መድረክ / ፎረም