በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን በሞያሌ ከተማ “ሸዋበር” በተባለ ቀበሌ የመኖሪያ መንደር የመከላከያ ሰራዊት አባላት በፈፀሙት ጥቃት ዐሥር ሰዎች ተገድለው ሌሎች ዐሥራ አንድ ሰዎች ቆስለዋል። ወደ 50 ሺሕ ነዋሪዎች መኖሪያ ቀያቸውን ጥለው ወደ አጎራባች ኬንያ ድንበር መሰደዳቸውን የከተማው ከንቲባ አስታውቀዋል።
በመንደሩ ውስጥ በሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ተኩስ በመክፈት ዐሥር ንፁኋን ዜጎችን የገደሉና ሌሎች ዐሥራ አንድ ያቆሰሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ድርጊቱን በፈፀሙበት የኦሮሚያ ክልል በመደበኛ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው እንዲታይ የከተማውና የዞኑ አስተዳደር ጠይቋል።
ይህንን ጥያቄም ለሚመለከታቸው ከፍተኛ ባልሥልጣናት አቅርበው ውይይት ማድረጋቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል። በሞያሌ ከተማ በመጋቢት 1/2010 ዓ.ም ከቀኑ አምስት ሰዓት እስከ ሰባት ሰዓት የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት በፈፀሙት ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውንና ሌሎች 12 ሰዎች መቁሰላቸው ኮማንድ ፖስቱ በሰጠው መግለጫም ማስታወቁ ይታወሳል።
የከተማው ከንቲባ አቶ አስቻለው ዩሃንስ ከቆሰሉት ውስጥ አንድ ሰው ሕይወቱ በማለፉ ሟቾቹ ዐስር መደረሳቸውን ተናገርዋል። ከቆሰሉት ውስጥ አምስቱ ወደ ሐዋሳ ሆስፒታል ለከፍተኛ ሕክምና መላካቸውና ሌሎች ስድስቱ ደግሞ በሞያሌ ከተማ ሆስፒታል ተንተው በመታከም ላይ ናቸው ብለዋል።
በሌላ በኩል የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አስፈፃሚ ኮማንድ ፖስት ሴክሬተሪያት ተወካይ ሌተናል ጄነራል ሃሰን ኢብራሂም ለመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ በሀገሪቷ የተፈጠረውን ሁኔታ ለማባባስ ያለመ የኦነግ ኃይል በሦስት አቅጣጫ ወደ አገሪቷ ሰርጎ ለመግባት ያደረገውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ወደ ሞያሌ የተጓዘ አንድ የሻለቃ ጦር የተሳሳተ መረጃ በመያዝ በተፈጠረ ግጭት የግዳጅ አፈጻጸም ደንቡን ባልተከተለ አኳኋን እርምጃ በመውሰዱ የሰው ህይወት ላይ ጉዳት መድረሱ ነው አስታውቋል።
የዞኑና የከተማው አስተዳደር በበኩላቸው ግድያው የተፈፀመበት ቦታ “ከኦነግ ጋራ ምንም የተገናኘ ነገር የሌለው ፍፁም ሰላማዊ የሆነ የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ነው። የተፈፀመው ድርጊትም ኢ- ሰብዓዊ በመሆኑ በመደበኛ ፍርድ ቤት እንዲታይ እንፈልጋለን” ብለዋል።
ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላ ወደ 50 ሺሕ ነዋሪዎች መኖሪያ ቀያቸውን ጥለው ወደ አጎራባች ኬንያ ድንበር መሰደዳቸውን የከተማው ከንቲባ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በትናንትናው ዕለት አንድ ነዋሪ በሞተር ሳይክል ላይ እያለ በጥይት ተመቶ መቁሰሉንና አንድ ነዋሪ ደግሞ ባልታወቀ ሁኔታ ሞቶ መገኘቱን ከንቲባ አቶ አቻለው ጨምረው ገልፀዋል።
ሙሉውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያገኛሉ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ