የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ግድያውን የፈፀሙት የአንድ የሻለቃ ጦር አዛዥ የሚገኝበት አምስት የሻለቃው ጦር አባላት ምድብ በያዙት የተሳሳተ መረጃ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አስፈፃሚ ኮማንድ ፖስት አመልክቷል።
ነዋሪዎችና የከተማው አስተዳደር “የአንድ ሀገር መንግሥት በራሱ ወታደር የራሱን ሀገር ሰላማዊ ዜጎችን በጭካኔ ገድሏል” ብለዋል።
የሞያሌ ከተማ ከንቲባ አቶ አስቻለው ዩሃንስ ለመነሻው የተጨበጠ ምክኒያት እንደሌለ ገልፀው የመጀመሪያውን ግድያ የተፈፀመው በአንድ የከተማው ነዋሪ ወጣት ላይ ነው ብለዋል። “የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ በሞተር ሳይክል እየሄደ የነበረን ወጣት አስቁመው በጥይት መተው ገደሉት” ብለዋል።
ወጣቱ ከሞተር ሳይክሉ ላይ እንዲወርድ የተደረገበትን ምክኒያት እንደማያውቁ የተናገሩት ከንቲባው፤ “አካባቢው ላይ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር አልነበረም ፤ ሕዝቡ በሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ነበር። ልጁን አውርደው መቱት ከዛ በኋላ ወደ መንደሩ እያዞሩ መተኮስ ጀመሩ።” ብለዋል።
ቀጥሎም ወደ መንደሩ ሰው በሙሉ ሲተኮስ እንደነበር ተናግረዋል። “እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ዐሥር ሰዎች ሞተዋል፣ ዐሥራ አንድ ሰዎች ቆስለዋል አምስቱ ሰዎች ወደ ሐዋሳ ለከፍተኛ ሕክምና ተልከዋል።” ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን በሞያሌ ከተማ “ሸዋበር” በተባለ ቀበሌ ውስጥ ያለው የመኖሪያ መንደር ምንም የተለየ ነገር የሌለው መደበኛ የሰዎች መኖሪያ እንደሆነ ጨምረው ተናግረዋል።
ከሟቾቹ መካከል “መዶ ሚጎ” በተሰኘ ትምሕርት ቤት ርእሰ መምሕር ይገኙበታል። አቶ ተማም ነጌሶ የ34 ዓመት ወጣት እንደነበር ጓደኞቹ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል። አቶ ተማም የአንድ ልጅ አባት ሲሆኑ ባለቤታቸው ወ/ሮ ኬሪያ አሕመድ ነፍሰጡር ናት።
ማምሻውን በስልክ ያነጋገርናቸው የመምሕሩ ጓደኞች፤ “ትናንትና ትምሕርት ቤት ከወላጅና መምሕራን ኮሚቴ ጋራ ስብሰባ ነበረው። ከስብሰባው በኋላ ለምሳ ወደ ቤቱ በመመለስ ላይ እያለ በአስፓልቱ በኩል ሊሻገር ሲል ነው የተመታው” ብለዋል። አያይዘውም፤ “መጀመሪያ ታፋውን ነበር የተመታው። ተነስቶ ሊሮጥ ሲል በድጋሚ በሌላ ጥይት ተመታና ወደቀ” ብለዋል።
ሌላው የመምሕሩ ጓደኛ፤ “በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ወደ ሦስት ቦታ ተደጋግሞ ነው የተመታው።ሕይወቱም ያለፈው እዚያው ነው” ብለዋል። “እንዲህ ያለ ድርጊት የሚፈፅመው ጠላት ነው” ያሉት የሟቹ ጓደኛ “እውነቱን ለመናገር በጠራራ ፀሐይ እያሳደደ ሕዝቡን የሚገድል መንግሥት የለም። ጠላት ነው እኛን እያሳደደን ያለው። መንግሥትን የሚዳኘው አካል ስለሌለ ወደ እግዚያብሔር እየጮህን ነው።” ብለውናል።
የሞያሌውን ሁኔታ በተመለከተ ከፌደራል ባለሥልጣናትና ከኮማንድ ፖስቱ መረጃን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ስልክ ስለማይነሳ ሊሳካል አልቻለም። ነገር ግን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አስፈፃሚ ኮማንድ ፖስት ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ፤ “በሀገረቱ የተፈጠረውን ሁከትና ግርግር እንደምቹ አጋጣሚ በመቁጠር ሁኔታውን ለማባባስና ለራሳቸው የጥፋት ሴራ ለማዋል በሞያሌ አከባቢ የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው የገቡ የኦነግ ታጣቂዎችን ለመቆጣጠርና ለመደምሰስ አንድ የሻለቃ ጦር በስፍራው ላይ ለግዳጅ ተሰማርቶ ይገኛል።” ካለ በኋላ
የሻለቃዋ ጦር አዛዥ የሚገኝበት አምስት የሻለቃዋ የሰራዊት አባላት የተሳሳተ መረጃ ይዘው ባደረጉት እንቅስቃሴ በአከባቢው ሕብረተሰብ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አስፍሯል።
የሞያሌ ከተማ ከንቲባ በበኩላቸው፤ “ ምን ከኦነግ ጋራ የተገናኘ ነገር የለም። አንደኛ ሕዝቡ የሚኖርበት ከተማ እንጂ ጫካ አይደለም። እኔ ኦነግ ከተማ ውስጥ ታጥቆ ስለሚሄድበት አጋጣሚ የማውቀው ነገር የለም። በአካባቢው በኬንያ አነግ አልፎ አልፎ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ይታወቃል። ተናንትና የተፈጠረው ግን ምንም ከኦነግ ጋራ የተገናኘ አንድም ነገር የለም” ብለዋል።
ሟቾቹ አብዛኞቹ ወጣቶች ሲሆኑ ሁሉም በጥይት ተመተው እንደተገደሉ ከንቲባው አረጋግጠዋል።
“የትም ሀገር ሕግና ሥርዓት አለ። ችግር የሚፈጥር አካል ካለ በሕግ ነው መጠየቅ ያለበት እንጂ በራሱ ወታደር በራሱ ዜጋ ላይ በጭካኔ የሚደረግ ነገር ለምንም ነገር መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ያለ ነገር ካለ በውይይት ነበር መፈታት ያለበት። ትናንት የተፈጠረው በጣም አሳፋሪና ነው። እንደ ከተማ ከንቲባ ይሄ ነገር አይደለም በዜጋ በጠላትም ላይ ይደረጋል የሚል እምነት የለኝም” ብለዋል ከንቲባው አቶ አስቻለው።
ኮማንድ ፖስቱ የዘጠኝ ሰው ሕይወት መጥፋቱንና ዐሥራ ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን የገለፀ ሲሆን ከንቲባው አቶ አስቻለው ከቆሰሉት መካከል አንዱ ሕይወቱ በማለፉ የሞቱት ዐሥር መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የሻለቃዋን አዛዥ ጨምሮ አምስቱ የሰራዊቱ አባላት ትጥቃቸውን ፈተው በቁጥጥር ስር ውለው የማጣራት ስራ
እየተካሄደባቸው እንደሆነ ያስታወቀው ኮማንድ ፖስቱ በአጋጣሚው ለጠፋው የሰው ህይወትና ጉዳት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገልጿል።
መቀመጫውን ብራስልስ ያደረገ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ለቪኦኤ በሰጡት ቃል “በዚህ ግድያ መጠየቅ ያለባቸው ድርጊቱን የፈፀሙት ብቻ ሳይሆኑ የኮማንድ ፖስቱ ኃላፊዎችና የሀገሪቱ የመከላከያ ኃላፊዎች በሙሉ ናቸው” ብለዋል።
አደጋውን ፈርተው ወደ ኬንያ ሞያሌ የተሻገሩት ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ፤ “ቁጥራቸው ያልታወቁ የሦስት ቀበሌ ነዋሪዎች ድንበር ተሻግረው ተጠልለዋል።” ብለውናል። ከተሰደዱበት ቦታ በስልክ ያነጋገርናቸው እናት “ዐሥራ ሦስት ልጆች አሉኝ። ታጣቂዎቹ በር በርግደው ስለሚገቡና ጥይት ስለሚተኩሱ “ምን ተፈጠረ?” ብሎ ለመጠየቅ እንኳን ጊዜ አይኖርም ስለዚህ ፈርቼ በሬን እንኳን ሳልዘጋ ሸሽቼ መጥቻለሁ። አሁን ባገኘሁበት አድሬያለሁ። ልጆቼን ግን የማበላው የለኝም።” ብለዋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ