ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ፣ በአንድ ነጭ ፖሊስ በአሠቃቂ ኹኔታ የተገደለበትና በመላው ዓለም የተካሔደው ከፍተኛ ተቃውሞ የተቀሰቀሰበት ሦስተኛ ዓመት ዛሬ ታስቧል።
በፍሎይድ ላይ የተፈጸመው ሥቅየት እና ግድያ፣ በፖሊስ አሠራር ውስጥ የተመሰገውን ዘረኝነት፣ አጋልጦ ያወጣ እንደነበር፣ በበርካታ ታዛቢዎች ዘንድ ይታመናል።
"መተንፈስ አልቻልኩም" የሚል ድምፅ ሲያሰማ የነበረውን የፍሎይድን አንገት በተኛበት ነጩ ፖሊስ ፤ ለስምንት ደቂቃ ከ46 ሰከንድ በጉልበቱ የተጫነበትን ምስል መመልከት በራሱ የአእምሮ ሥቅየት ነበር።
ክሥተቱ፣ በመላ አገሪቱ የፖሊስ ኃይሉ የአሠራር ለውጥ እንዲያደርግ የተጠናከረ ጥያቄ አነሣስቷል። ኾኖም፣ በጊዜው የተስፋፋው የኮሮና ወረርሽኝ እና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ የታለመው ለውጥ እንዳይደረግ ትኩረትን አናጥቧል።
ፖሊስ፥ አንገትን ማነቅንና ድንገት የሰው ቤት መምጣትን የመሰሉ ድርጊቶቹን እንዲያቆም የሚወተውቱ ወገኖች፣ አሁንም፣ በፖሊስ አሠራር ውስጥ ለውጥ እንዲኖር በመጠየቅ ላይ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በዋሽንግተን ግዛት ታኮማ ከተማ፣ ከአራት ዓመታት በፊት በአንድ ፖሊስ በአሠቃቂ ኹኔታ በሰባት ጥይት ተደብድቦ ሕይወቱ ላለፈው ጥቁር አሜሪካዊው ቢኒ ብራንች ቤተሰብ፣ የከተማ አስተዳደሩ 3ነጥብ1 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፍል አስታውቋል።
መኪናው፣ በተቃራኒ አቅጣጫ በመቆሙ ምክንያት ከፖሊስ ጋራ የተገናኘው ቢኒ፣ ሽጉጥ ሳይዝ አይቀርም፤ በሚል፣ አንድ የፖሊስ አባል 11 ጊዜ ተኩሶ፣ ሰባት ጊዜ መቶታል።
ከግድያው በኋላ በተደረገው ማጣራት፣ ሟቹ ይዞት የነበረው የዒላማ መለማመጃ፣ ሐሰተኛ ሽጉጥ እንደነበር ታውቋል።