በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በፍሎይድ ሞት የተከሰሱት የቀድሞ ፖሊስ “ደንብ ጥሰዋል” ተባለ


 በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን በጆርጅ ፍሎይድ አሟሟት የተከሰሰውን የቀድሞ ፖሊስ መኮንን ችሎት ላለማየት ባለፈው ሳምንት አርብ ተዋናዩ ስቲቨን ቶምፕሰን በሎስ አንጀለስ ከሚገኘው የጆርጅ ፍሎይድ ምስል አጠገብ በመቆም ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን በጆርጅ ፍሎይድ አሟሟት የተከሰሰውን የቀድሞ ፖሊስ መኮንን ችሎት ላለማየት ባለፈው ሳምንት አርብ ተዋናዩ ስቲቨን ቶምፕሰን በሎስ አንጀለስ ከሚገኘው የጆርጅ ፍሎይድ ምስል አጠገብ በመቆም ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

ባለፈው ዓመት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዳለ ህይወቱ ባለፈው ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ህልፈት በተከሰሱት የቀድሞ ፖሊስ መኮንን ዴሪክ ሻቭን ላይ ክስ የመሰረቱት አቃቢ ህጎች የክሶቻቸውን ጭብጥና ክርክር ለችሎቱ ማሰማት ከጀመሩ ትናንት ሰኞ ሁለተኛ ሳምንቱ ተቆጥሯል፡፡

የምኒያፖሊሱ የፖሊስ ዋና አዛዥ ትናንት ሰኞ ከህዝብ ለተውጣጡ ዳኞች ወይም ጁሪዎች እንዳስታወቁት የቀድሞ የፖሊስ መኮንን ዴሪክ ሻቭን ጆርጅ ፍሎይድን በቁጥጥር ስር ሲያውሉ የፈጸሙት ነገር “የፖሊስ መምሪያውን አያያዝ ደንብ የተከተለ አይደለም” በማለት ተናግረዋል፡፡

የፖሊስ አዛዡ የፖሊስ መኮንኑ ለመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሰክንዶች ሟችን በቁጥጥር ስር ለማድረግ የተጠቀመበት መንገድ አግባብነት ያለው ነው ካሉ በኋላ፣ “ይሁን እንጂ ሚስተር ፎሎይድ ምንም ተቃውሞ ማሳየት ቀርቶ መንቀሳቀስ እንኳ ባቆሙበት ሰዓት፣ እንደዚያ ያለውን የኃይል መጠን፣ መጠቀሙን መቀጠል፣ በየትኛም መንገድ ቢሆን መመሪያችንም ሥልጠናችንም፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሥነምግባርና ሞራላችንም የሚፈቅደው ነገር አይደለም፡፡” ብለዋል፡፡

ሻቭን የተከሰሱት በጆርጅ ፍሎይድ አንገት ላይ ጉልበታቸውን ከ9 ደቂቃዎች በላይ በመጫን፣ ወይም በማነቅ ለፎልይድ ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆነዋል ተብለው ነው፡፡

በትናንትው እለት ዳኞቹም ሲያደምጡ የዋሉት አንገትን ስለማነቅና ስለመታፈን ክርክር ነው፡፡

የሜኒሶታ ፖሊስ ዋና አዛዥ ሜዳሪያ አረዶንዶ እንዲህ ይላሉ

“በፖሊስ አያያዝ የተጠቀሰው አንገትን የማነቅ ሁኔታ ጥንቃቄ በተሞላበት ከቀላል እስከ መካከለኛ ጫና ማሳደር ድረስ የሚሄድ ነው፡፡ በኤግዚቢት 17 ላይ በማስረጃነት የቀረበውን የጆርጅ ፍሎይድ የፊት አገላለጽ ሁኔታ ስመለከት የተደረገው በየትኛው መንገድ ወይም ቅርጽ ከቀላል እስከ መካከለኛ ድረስ ያለውን ጫና አይመስልም፡፡”

የህክምና ባለሙያዎች የፍሎይድ ልብ ሆስፒታል ከመድረሱ በፊት የቆመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እኤአ ግንቦት 25/ 2020 በሆስፒታሉ አስቸኳይ ህሙማን መቀበያ ክፍል ፍሎይድን የተቀበሉት ዶክተር ለዳኞቹ እንደተናገሩት ፍሎይድን ለህልፈት ያበቃው የኦክስጂን እጥረት ነው፡፡

በፍሎይድ ሞት የተከሰሱት የቀድሞ ፖሊስ “ደንብ ጥሰዋል” ተባለ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:10 0:00


ከሄንፕን ካውንቲ ሜዲካል ሴንተር በዐቃቢ ህጉ ፍሎይድ ህይወቱ ያለፈው “በኦክሲጅን እጥረት ሳቢያ ልቡ ደም መርጨት በማቆሙ ነው ?” ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ብራድፍሮድ እንዲህ ብለዋል

“ያ በጣም ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከሌሎቹ ይልቅ በዚያ ሰዐት በነበረኝ መረጃ መሰረት የተሰማኝ ነገር ቢኖር ያ መሆኑ ነው፡፡”

በኦክስጅን ወይም ትንፋሽ እጥረት ምክንያት የሚከሰትን ሞት የምትጠሩበት ሌላ መጠሪያ አላችሁ ተብለው በአቃቢ ህጉ የተጠየቁት ዶ/ር ብራድፎርድ፣ “አስፓያክሲያ” የሚለው ቃል የተለመደው አገላለጽ ነው በማለት መልሰዋል፡፡

የተከላካይ ጠበቆች ግን ፍሎይድ የሞተው ከዚህ ባልተገናኘ ሌላ የጤንነት ጉድለት እንዲሁም ከአደገኛ መድሃኒትና እጽ ጋር የተያያዘ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ፈንታሊን እና ሜታፈታማይን የተባሉ አደገኛ መድሃኒትና ህጾች በፍሎይድ ሰውነት ውስጥ የነበሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የዴሪክ ሻቭን ጠበቃ ኤሪክ ኒልሰን ይህንኑ መሠረት በማድረግ በምስክርነት ለቀረቡት ዶ/ር ብራድሮድ ጥያቄዎችን አቅርበዋል

“ስለዚህ ሃይፓክሲያ የሚባለው፣ በደም ውስጥ በቂ ኦክሲጅን እንዳይዘዋወር፣ ሰውነት ሥራውን በብቃት እንዳይሰራ፣ የሚያደርጉ ምክንያቶች፣ እንደ መታፈን ወይም አስፋይክሴሽን ተደርገው የሚወሰዱ በርካቶች አይደሉም?

ሀኪሙ “አዎ ትክክል” በማለት መለሱ ፡፡

የተከላካዩ ጠበቃ አሁንም ሌላ ጥያቄ አቀረቡ

“ይህን በሰውነት ኦክሲጂን እንዳይኖር የሚያደርጉ የተለያዩ አደገኛ መድሃኒቶችና ህጾችም አሉ አይደለም?”

አሁንም ሀኪሙ “አዎ” አሉ ደግመው፡፡

ባለፈው ዓመት ህይወቱ ያለፈው ጆርጅ ፍሎይድ የፖሊሶችን ስልጠና ዓላማና ድርጊት “የጥቁርም ህይወት ዋጋ አለው” በሚል የተነሳውን ተቃውሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲቀጣጠል ማድረጉ ይታወሳል፡፡

የቪኦኤ ዘጋቢ ኢሻ ሳራዬ ካጠናቀረችው ዘገባ የተወሰደ፡፡

XS
SM
MD
LG