በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ የተከሰሰው ፖሊስ የክስ ሰሚ ችሎት ቀጥሏል


በዩናይትድ ስቴትስ ሚኔሶታ ክፍለ ግዛት ሚኒያፖሊስ ከተማ ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድን በመግደል ክስ የተመሰረተበት ፖሊስ ዴሬክ ሾቭን ክስ ሂደት ዛሬ ሦስተኛ ቀኑን ይዟል።

ፍሎይድን ባለኝ የጤና እርዳታ ሥልጠና ልርዳው ብትል ፖሊሶቹ እንዳልፈቀዱላትና በዚያም ምክንያት እንደተበሳጨች ትናንት ማክሰኞ ለክስ ሰሚው ችሎት የምስክርነት ቃሏን የሰጠችው የእሳት አደጋ ሰራተኛ ጂኒቪቭ ሃንሰን ዛሬም ቃሏን ትሰጣለች።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ሚኒያፖሊስ ከተማ በሚገኝ መደብር ደጃፍ ፖሊሱ ዴሬክ ሾቪን ጆርጅ ፍሎይድን መሬት አስተኝቶ አንገቱን በጉልበቱ ተጭኖት ማየታቸው እንዳበሳጫቸው እና እንዳስቆጣቸው የገለጹ ሊሎችም ዕማኞች ቀርበው ቃላቸውን ሰጥተዋል።

በዕማኞች እና በቦታው የነበሩ ሰዎች በቀረጹት የቪዲዮ ምስሎች መሰረት ጂኔቪቭ ሃንሰን ጆርጅ ፍሎይድን በቁጥጥር ስር ላዋሉት ፖሊሶች የእሳት አደጋ ሰራተኛ መሆኑዋን ገልጻላቸው የፍሎይድን የልብ ምት ለምርምር ብላ በተደጋጋሚ ጠይቃቸው ነበር።

ፖሊሱ ዴሬክ ሾቭን ለዘጠኝ ደቂቃ ከሃያ ዘጠኝ ሰኮንድ በጉልበቱ አንገቱን ተጭኖት እንደነበር አቃቤ ህጎች ለችሎቱ ተናግረዋል።

ዴሬክ ሾቭን የተለያዩ የግድያ ወንጀል ክሶች ተመስርተውበታል። ወንጀሉን አልፈጸምኩም ብሎ ቃሉን ሰጥቷል። የሾቭን ጠበቆች በበኩላቸው "ፖሊሱ በተፈጠረው ድንገት የሙያ ስልጠናውን ተከትሏል፥ ፍሎይድን ለህልፈት ያበቃው የልብ ህመም እና ሱስ አስያዥ መድሃኒት ተጠቃሚነቱ ነው "ሲሉ ተከራክረዋል።

የጆርጅ ፍሎይድ ሞት እና በድንገቱ ዙሪያ በማህበራዊ መገናኛ የተሰራጩትን የቪድዮ ምስሎችና እና የዜና ዘገባዎች ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ እና በሌሎችም የዓለም አካባቢዎች የፖሊሶች የጭካኔ አድራጎቶችን በመቃወም ሰልፎች መካሄዳቸው የሚታወስ ነው።

በቅርቡ የሚኒያፖሊስ ከተማ አስተዳደር ለጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰብ ሃያ ሰባት ሚሊዮን ዶላር የጉዳት ካሳ ሊከፍል ተስማምቷል።

XS
SM
MD
LG