ከፑንትላንድ ሶማልያ የተነሱ ሃይሎች ባለፈው ሰኞ በአከባቢው የባህር ጠርፍ መንደሮች በገቡት የአል-ሸባብ አማጽያን ላይ ጥቃት እንደከፈቱ ባለሥልጣኖችና እማኞች ተናግረዋል።
የፑንትላንድ የማስታወቅያ ሚኒስትር ሞሐሙድ ሐሰን ሶዐዴ የግዛቲቱ የጸጥታ ሀይሎች ከደባባዊ ሶማልያ ተነስተው ፑንትላንድን ወረሩ ባልዋቸው የአል-ሸባብ አማጽያን ላይ ጥቃት ከፍተዋል ሲሉ በፑንትላንድ መዲና ጋሮዌ ላይ ባካሄዱት ጋዜጣዊ ጉባኤ ገልጸዋል።
የአከባቢው ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምጽ ዘጋቢ በተናገሩት መሰረት ሱጅ (Suuj) በተባለው በኑጋል ክልል የሚገኝ ወንዝ ያለበት አከባቢ ከባድ ውጊያ ቀጥሏል።
አከባቢው የባህር ላይ ዘራፊዎች መናኸርያ እንደነበር ተገልጿል። የማስታወቅያው ሚኒስትር የፑንትላንድ ወታደሮች ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ገልጸው በርካታ አማጽያን ተገድለዋል ብለዋል። አል ሸባብ እስካሁን ባለው ጊዜ ስለ ውጊያው የተናገረው ነገር የለም። አንዳሉስ የተባለው በሶማልያ የሚተላለፈው የአል-ሸባብ አፈ-ቀላጤ የሆነ ሬድዮ “የሙጂሐዲን ሀይሎች ፑንትላንድ ውስጥ አዳዲስ ግዛቶችን ይዘዋል” ሲል ትላንት ተናግሮ ነበር።