ዋሽንግተን ዲሲ —
በግብጽ ሁከታማ በሆነው የሲናይ ልሳነ ምድር ታጣቂዎች በፍተሻ ኬላ ላይ ተኩስ ከፍተው አምስት ፖሊሶች መግደላቸውን የአገር አስተዳደር ሚኒስቴሩ አስታወቀ።
የሲናይ ትልቋ ከተማ በሆነችው ኤል አሪሺም ትናንት ረቡዕ ማታ በደረሰው ጥቃት ሶስት ፖሊሶች መቁሰላቸውን ሚኒስቴሩ አመልክቷል። ለጥቃቱ ሃላፊነት የወሰደ ወገን ግን የለም።
ግብጽ እአአ በ2013 ዓ. ም. እስላማዊው ፕሬዚደንት ሞሃማድ ሞርሲ በጦር ሰራዊቱ ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ ታጣቂዎችን ስትታገል ቆይታለች።
ለሚደርሱት ለአብዛኞቹ ጥቃቶች የእስልምና መንግሥት ብሎ ራሱን የሚጠራው ቡድን ግብረ አበር የሆነ ታጣቂ ቡድን ሃላፊነት ሲወስድ ቆይቷል። የዜና ዘገባውን ለማዳመጥ የድምጽ ፋይሉን ይጫኑ።