በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጋዜጠኞችን በማሰር ቻይና በዓለም አንደኛ ሃገር መሆኗን ሲፒጄ አስታወቀ


ፋይል ፎቶ - [አሶሽየትድ ፕረስ/ AP]
ፋይል ፎቶ - [አሶሽየትድ ፕረስ/ AP]

ጋዜጠኞችን በማሰር ቻይና በዓለም አንደኛ ሃገር መሆኗን ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ቡድን - ሲፒጄ አስታወቀ። ቡድኑ ዛሬ ባወጣው ሪፖርት በዓለም ዙሪያ የጋዜጠኞች እሥራት በመጠኑ መቀነሱንም አክሎ አመልክቷል።

በዓለም አቀፉ የፕሬስ ነፃነት ተሟጋች ቡድን ሪፖርት መሠረት በዓለም ዙሪያ ጋዜጠኞችን በማሠር ቻይናና ግብፅ አቻ የላቸውም።

ቻይና እንዲያውም ዘንድሮ 49 ጋዜጠኞችን አሥራ ባለፈው ዓመት ይዛው የነበረውን የቀዳሚነት ቦታ በድጋሚ ተቆጣጥራ ባሠረቻቸው ጋዜጠኞች ቁጥርም የራሷን የአምና ሪከርድ ሰብራለች።

ሁለቱ ሃገሮች መንግሥቱን ይቀናቀናሉ ብለው የሚገምቷቸውን ዘገባዎች ሁሉ ለመቆጣጠር ብርቱ ጥረት የሚያደርጉ ሃገሮች መሆናቸውንም ሲፒጄ አክሎ ጠቁሟል።

በዓለም ዙሪያ በዚህ እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓ 2015 ዓመት ባለፉ አሥራ አምስት ቀናት ውስጥ በሃያ ስምንት ሃገሮች 199 ጋዜጠኞች ታስረው የሚገኙ ሲሆን ይህ ቁጥር ባለፈው ዓመት ተመሣሣይ ጊዜ 221 እንደነበረ ሲፒጄ አስታውቋል።

ቻይና ጋዜጠኞቿን በዚህ ዓመት ያሠረችው በከፊልም እየተዳከመ ባለው ምጣኔ ኃብቱ ላይ በሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ሆደ ባሻ እየሆነች በመምጣቷ መሆኑን ቡድኑ ጠቁሟል።

የቻይና ትችትን የማፈን አባዜ ዩናይትድ ስቴትስንም መንካቱን የገለፀው የዛሬው የስፒጄ ሪፖርት ዋና መሥሪያ ቤቱ ዋሺንግተን ዲሲ የሆነውና የቪኦኤ እህት የዜና አውታር የራዲዮ ፍሪ ኤዥያ ባልደረባ ሾሬት ሆሹር ቻይና ውስጥ እርሱ የወጣበት ጎሣ የሆኑት ሕዳጣኑ ዩጉሮችን አያያዝ ተችቶ በመፃፉ የቻይና ባለሥልጣናት ሦስት ወንድሞቹን በቁጥጥር ሥር ያዋሉት መሆኑን አመልክቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ “የግብፁ ችሬዚዳንት አብደል ፋታህ ኤል ሲሲ የሃገር ደኅንነትን አጀንዳ እንደሰበብ በመቁጠር ተቃውሞን የማፈን አድራጎታቸውን ቀጥለዋል” የሚለው ሲፒጄ ካይሮ በአሁኑ ጊዜ 23 ጋዜጠኞችን አሥራ እንደምትገኝ አስታውቋል።

ሲፒጄ ለንፅፅር ባወጣው መረጃ “የዛሬ ሦስት ዓመት እኮ ግብፅ ውስጥ በሥራው ምክንያት የታሠረ አንድም ጋዜጠኛ አልነበረም” ብሏል።

ኢራን ጋዜጠኞችን ለማሠር የምትጠቀምበት ሰበብ “ፀረ-መንግሥት አድራጎት” የሚል መሆኑን፤ ነገር ግን ያሠረቻቸው ጋዜጠኞች ቁጥር ባለፈው ዓመት ከነበረው 30 ዘንድሮ ወደ 19 መውረዱን ሲፒጄ ተናግሯል።

ኢራን ካሠረቻቸው ጋዜጠኞች መካከል በስለላ ተግባር ክሥ ተመሥርቶበት እንደተፈረደበት የተነገረው አሜሪካዊው የዋሺንግተን ፖስት ዘጋቢ ጄሰን ሬዛያን እንደሚገኝበት ሲፒጄ አመልክቶ ሬዛያን ከተያዘ አምስት መቶ ቀናት ያለፉት መሆኑን ከመጠቆም ያለፈ ዝርዝር እንደሌለ ገልጿል።

የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋቹ ቡድን በዛሬው ሪፖርቱ “በፍርድ ሂደት አያያዟ ብልሹነት በዓለም አቻ የሌላት ናት” ባላት ኤርትራ የወንጀል ክሥ በይፋ ሳይመሠረትባቸው ወይም ችሎት ፊት ሳይቀርቡ 17 ጋዜጠኞች ታስረው እንደሚገኙ አመልክቷል።

ኤርትራ በዚህ የአውሮፓ ዓመት በመንግሥቱ ይዞታ ሥር የሚገኘው የራዲዮ ባና ባለደረቦች የነበሩ ስድስት ጋዜጠኞችን በይፋ ባልተገለፀ ምክንያት ከእሥር መፍታቱን ሲፒጄ ገልጿል።

ኢትዮጵያ እጅግ የጠነከረ ቅድመ-ምርመራ ካለባቸው ሃገሮች አንዷ መሆኗን የሚናገረው ሲፒጄ በዚህ ዓመት የዞን ዘጠኝ አባላት የሆኑ ስድስት ብሎገሮችን ብትለቅቅም በኢንተርኔት ላይ በመፃፍ የሚታወቀው እስክንድር ነጋ በሽብር ክሥ የ18 ዓመት እሥራት ተፈርዶበት አሁንም ወኅኒ እንደሚገኝ አመልክቷል።

ሌላው አስተያየት ፀሐፊ ተመስገን ደሣለኝም እንዲሁ የጎበኙት ሰዎች እንደሚሉት የሕክምና አገልግሎት ተነፍጎት እሥር ቤት ውስጥ እንደሚገኝ ሲፒጄ አክሎ በሪፖርቱ ላይ ተናግሯል።

ቱርክ 14 ጋዜጠኞችን ማሠሯን የጠቆመው ሲፒጄ ሁለቱ ጋዜጠኞች የተያዙት የአንካራ የስለላ መዋቅር ወኪሎች የጦር መሣሪያ በሰብዓዊ ዕርዳታ ስም ወደ ሶሪያ ማሸጋገራቸውን ጠቁመው ላወጡት ዘገባ በስለላ አድራጎት መሠማራት የሚል ክሥ ተመሥርቶባቸው መሆኑን ሲፒጄ ጠቁሟል።

ዘገባውን ለማዳመጥ ከዚህ በታች ያለውን የድምጽ ፋይል ያዳምጡ።

ጋዜጠኞችን በማሰር ቻይና በዓለም አንደኛ ሃገር መሆኗን ሲፒጄ አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:15 0:00

XS
SM
MD
LG