በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እድገት ለሚቀጥለው አንድ ዓመት እንደሚያሽቆለቁል የዓለም የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ አስታወቀ


የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እድገት ለሚቀጥለው አንድ ዓመት እንደሚያሽቆለቁል የዓለም የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ አስታወቀ
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እድገት ለሚቀጥለው አንድ ዓመት እንደሚያሽቆለቁል የዓለም የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እድገት ለሚቀጥለው አንድ ዓመት እንደሚያሽቆለቁል የዓለም የገንዘብ ድርጅት IMF አስታወቀ። በዚህ በያዝንው የአውሮፓዊያን ዓመት 2016 የኢትዮጵያ ሀገራዊ ሀብት ምጣኔ በ4.5 ከመቶ እንደሚያድግ የገንዘብ ድርጅቱ ተንብይዋል።ከአስርት ዓመታት በላይ ወደ ሁለት ዲጂት የሚጠጋ እድገት ሲያሳይ የቆየው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት በፍጥነት እንዲያሽቆለቁል ያደረገው በሀገሪቱ የተከሰተው ድርቅና የዓለም አቀፍ የሸቀጥ ገበያ ዋጋ መቀነስ እንደሆነ ታውቋል።​

በዓለም በፍጥነት በማደግ ላይ ከነበሩ አስራ ሀገሮች ሰባቱ የአፍሪካ ሀገሮች ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሆና ቆይታለች። የያዝንው የአውሮፓዊያን ዓመት ግን ይሄ ሁኔታ እንደሚቀየር ነው የዓለም የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ (IMF)በየዓመቱ የሚያወጣው የዓለም ምጣኔ ሀብት ግምገማ ዘገባው አስታውቋል።

ባለፈው ዓመት 10.2 ከመቶ ያደገው ምጣኔ አሁን በያዝንው ዓመት 4.5 ከመቶ የሀገራዊ ምርት እንደሚኖር ድርጅቱ አስታውቋል።

የዓለም የገንዘብ ድርጅት ጥናት ቡድንን የመሩት ኦያ ሴላሰን፤ በምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገሮች የምጣኔ ሀብት ትንበያ ላይ ጉልህ ተጽኖ ያሳደሩ ሁኔታዎችን እንዲህ አስረድተዋል።

"አንዱ ምክንያት ምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ብርቱ ድርቅ ተከስቶባቸምብዋል። የዝናብ መጠኑ ለበርካታ ዓመታት ከተመዘገበው አማካይ በ40 ከመቶ ቀንሷል። ይሄ ሁኔታ በምጣኔ ሀብት እድገት ትንበያው ላይ ተንጸባርቋል፤ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ምጣኔ ሀብቶችን ጎድቷል። ማላዊ፣ ዝምባብዌ፣ ዛምቢያና ደቡብ አፍሪካንም ጎድቷል።" ብለዋል።

የዓለም የገንዘብ ድርጅት አርማ
የዓለም የገንዘብ ድርጅት አርማ

የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዙ በአፍሪካ አማካይ እድገትም ተመዝግቧል። ባለፈው ዓመት በ3.4 ከመቶ ያደገው የአፍሪካ ምርት በያዝንው ዓመት ወደ 3ከመቶ ዝቅ እንደሚል ነው፤ የዓለም የገንዘብ ድርጅት የተነበየው። በተለይ በአፍሪካ እንደ ናይጀሪያ፣ አንጎላ፣ ደቡብ ሱዳንና ሌሎች የነዳጅ ዘይት አምራች ሀገሮች በነዳጅ ዘይት ዋጋ መቀነስ ሳቢያ ምጣኔያቸው ተንኮታኩቷል።

የዓለም የገንዘብ ድጅርትን ጥናት የመሩት ኦያ ሴላሰን "የነዳጅ ዘይት አምራች ሀገሮች አሉ፣ ነዳጅ የማያመርቱ ግን በዓለም የሸቀጥ ገበያ በቀጥታ የሚሳተፉ ሀገሮችም አሉ። በስፋት በሸቀጥ ገበያው የማይሳተፉ ሀገሮችም እንዲሁ በርካታ ናቸው። የነዳጅ ዘይት ዋጋና የሌሎች ሸቀጦች ዋጋ ሲቀንስ የሀገሮቹ ምጣኔም አብሮ ይታወካል። በእርግጥ ሁኔታውን ለመለወጥ የጀመሯቸው በርካታ ውጥኖች አሉ። ሆኖም ምጣኔ ሀብታቸውን መጎዳቱ አልቀረም። ለዚህ ነው በሚቀጥለው ዓመት የምጣኔ ሀብታቸው እድገት ትንበያ አሉታዊ ተጽኖ ያሳደረውል።" በማለት ለአሜሪካ ድምጽ ሃሳባቸውን ገልጸዋል።

የዓለም ባንክ አርማ
የዓለም ባንክ አርማ

በድርቅ የተነሳ ጉዳይ ያልደረሰባቸው የአፍሪካና የዓለም ሀገሮች፤ በተለይ የነዳጅ ዘይት አምራች ያልሆኑት በዚህ ዓመት የተሻለ የምጣኔ ሀብት እድገት ትንበያ አግኝተዋል። ሆኖም የዓለም ምጣኔ ሀብት ባለው ትስስር የተነሳ በተዘዋዋሪ እድገታቸው ላይ አሉታዊ ተጽኖ ሊኖረው እንደሚችል ነው የIMF ጥናት ያስቀመጠው።

"የዓለም አቀፍ የሸቀጥ ገበያ ተጽኖ የማያሳድርባቸው ሀገሮች በሁኔታው ክፉኛ አልተጎዱም። ሆኖም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ገበያና የመዋእለንዋይ ፍሰት ስለሚደርቅ፤ በተዘዋዋሪ በተለይ በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ምጣኔ ሀብቶች ላይ ተጽኖ እንደሚያሳድር በጥናታችን ተንጸባርቋል።" ብለዋል።

በዓጠቃላይ የዓለም ምጣኔ ሀብት በዚህ በያዝንው ዓመት በ3.2 ከመቶ እንደሚያድግ ተገልጿል። ቀጣዩ የአውሮፓዊያን ዓመት 2017 በተለይ የተሻለ የእድገት ዘመን እንደሚሆን ነው ጥናቱ የጠቆመው። ለኢትዮጵያ ምጣኔም ከዘንድሮው የተሻለ እድገት እንደሚጠበቅ ትንበያው ያስረዳል።

ዘጋቢያችን ሔኖክ ሰማእግዜር የአመታዊው የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ (IMF)ጉባዔ ላይ ተገኝቶ ያጠናቀረውን ዘገባ ለማዳመጥ የድምጽ ፋይሉን ይጫኑ።​

ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG