በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል፣ ባለፈው ዓመት ጥቅምት በፕሪቶርያ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት የስልታዊ ሂደት ግምገማ መጀመሩን የአፍሪካ ኅብረት አስታወቀ።
ግምገማው፣ የሰላም ሒደቱ “ወሳኝ ነጥቦች” በተባሉት፥ የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት፣ የትጥቅ መፍታትና የድኅረ ጦርነት መልሶ ግንባታ ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ፣ የኅብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች የሰላም እና ጸጥታ ኮሚሽን ገልጿል።
የፌደራሉ መንግሥት እና የትግራይ ክልል ተወካዮች እንዲሁም ታዛቢዎች፣ በግምገማው ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
ለሁለት ዓመት ገደማ የተካሔደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተቋጨበትንና ባለፈው ዓመት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በፌዴራሉ መንግሥት እና በህወሓት መካከል በፕሪቶርያ-ደቡብ ኣፍሪካ የተፈረመውን ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነት አፈጻጸም አስመልክቶ፣ “ስትራቴጂካዊ ግምገማ” ማካሔድ መጀመሩን የአፍሪካ ኅብረት አስታውቋል፡፡
የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የሚካሔድ የመጀመሪያ የአፈጻጸም ግምገማ እንደኾነ የገለጸው፣ የኅብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች የሰላም እና ጸጥታ ኮሚሽን፣ የሰላም ሒደቱ “ወሳኝ ነጥቦች” ናቸው ባላቸው በሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት፣ በትጥቅ መፍታት፣ በድኅረ ጦርነት መልሶ ግንባታ እና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር አስረድቷል፡፡
ግምገማው፣ የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪ ልኡካን የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ እና የቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ባሉበት በዝግ መካሔድ ጀምሯል፡፡
ፌደራል መንግሥቱን በመወከል የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዲሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ እና ሌሎችም ሲገኙ፤ በህወሓት በኩል ደግሞ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ እና የህወሓት ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልን ጨምሮ ሌሎችም በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
ከታዛቢዎቹም፣ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመርንና የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮችን ጨምሮ ሌሎችም አካላት የውይይቱ ተሳታፊዎች ናቸው።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማሃመት፣ በግምገማው መክፈቻ ላይ ባቀረቡት ገለጻ፣ “የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በመፈረሙ ግጭት ቆሟል፤ ከባድ እና መካከለኛ የጦር መሣሪያዎች ርክክብ ተፈጽሟል፤ መሠረታዊ አገልግሎቶች ዳግም ተጀምረዋል፤ በአብዛኛው የትግራይ ክልል አካባቢዎች ደግሞ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና ትምህርት ተጀምሯል፤” ማለታቸውን ኅብረቱ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡
የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ጥረት አድርገዋል ያሏቸውን ተቋማት እና ሀገራት ሊቀ መንበሩ ማመስገናቸውን ጠቅሷል፡፡ በቀጣይ የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም፥ ፖለቲካዊ ውይይት፣ የሽግግር ፍትሕ እና የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ኅብረተሰቡ የማዋሐድ ሥራ፣ ትግበራቸው በአፋጣኝ እንዲጀመር የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር በአጽንዖት ያነሧቸው ጉዳዮች እንደኾኑም ገልጿል፡፡
ከውይይቱ ምን ዓይነት ውጤት እንደሚጠብቁ የአሜሪካ ድምፅ የጠየቃቸው በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር የማነ ካሳ፣ ስምምነቱን በፈረሙ አካላት መካከል መተማመንና ቅንነት አለ ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል ፡፡
አደራዳሪዎች እና ታዛቢዎች፣ የሰላም ስምምነቱ በሙሉ ቃሉ እና መንፈሱ እንዲተገበር ሁለቱንም ወገኖች መገፋፋትና መደገፍ እንደሚጠበቅባቸው ያስገነዘቡት ተባባሪ ፕሮፌሰር የማነ፣ “ታጣቂን መበተን” በሚለው ላይ ብቻ አተኩረው እንደሚናገሩ በመጥቀስ ተችተዋል፡፡
የመብቶች ተሟጋች የኾነው “ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ” ድርጅት ምክትል ዲሬክተር አቶ መብርሂ በርሀ፣ ግምገማው፡- “ተፈናቃዮች በሚመለሱበት፣ ተጎጂዎች ፍትሕ በሚያገኙበትና ታጣቂዎች ትጥቅ በሚፈቱበት ጉዳይ ላይ አተኩሮ ይወያያል፤” ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመበት ጊዜ በ16 ወራት ዘግይቶ እየተካሔደ ያለ ግምገማ እንደኾነ አቶ መብርሂ አውስተው፣ መድረኩ፣ ስምምነቱ በምልኣት የሚተገበርበትን ኹኔታ ካላመቻቸ፣ ወደ ሌላ ግጭት እንዳይገባ ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
የፕሪቶርያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የሚካሔደው ይኸው የአፈጻጸም ግምገማ፣ የመጀመሪያ እንደኾነ የአፍሪካ ኅብረት አስታውቋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ ሰሞኑን በድረ ገጹ ባወጣውና የልዩ መልዕክተኛውን ማይክ ሐመር ጉዞ ባስታወቀበት መግለጫው፣ ጦርነቱ ያበቃ ቢኾንም ሰላሙን ለማጽናት ተጨማሪ ርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥቷል፡፡
ዛሬ የተጀመረውን የሰላም ስምምነቱን የአፈጻጸም ግምገማ አስመልክቶ፣ ከፌደራሉ መንግሥትም ኾነ ከትግራይ ክልል በኩል፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በይፋ የተባለ ነገር የለም፡፡
መድረክ / ፎረም