በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች ሰላም ዘላቂነት ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዲኾን ተጠየቀ


ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች ሰላም ዘላቂነት ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዲኾን ተጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:34 0:00

ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች ሰላም ዘላቂነት ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዲኾን ተጠየቀ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች፣ በሸማቂዎች እና በመንግሥት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሰፈነው መረጋጋት ዘላቂ እንዲኾን፣ ሁለቱም ወገኖች ቃላቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው፣ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋትሉዋክ ሮን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የሁለቱም ክልሎች አንዳንድ ነዋሪዎች፣ በክልሉ የሰፈነው ሰላም እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

በሁለቱም ክልሎች፣ ከዚኽ ቀደም በሽምቅ ውጊያ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ የሸማቂዎቹ መሪዎች፣ ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ ከመንግሥት ጋራ እንደሚሠሩ ማሳወቃቸው ይታወሳል።

የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ጉሕዴን/ ሊቀ መንበር አቶ ግራኝ ጉደታ፣ በወርኀ ጥቅምት 2015 ዓ.ም.፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋራ የሰላም ስምምነት ፈርመው፣ ከአንድ ሺሕ በላይ የሚኾኑ ታጣቂዎቻቸው፣ ከጫካ ተመልሰው በምሕረት እና ይቅርታ ከኅብረተሰቡ ጋራ ከተቀላቀሉ ወዲህ፣ ከመንግሥት ጋራ በሰላም እና በልማት ዙሪያ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ በወርኀ ታኅሣሥ 2015 ዓ.ም.፣ ከመንግሥት ጋራ ስምምነት ላይ ደርሶ የተመለሰው የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/ቤሕነን/፣ ከስምምነቱ ወዲህ ሰላም በክልሉ መውረዱ ተጠቁሟል።

የካማሽ ዞን ካማሽ ከተማ ነዋሪ የኾኑት አቶ ዋስይሁን ሰንበታ፣ “ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ፣ ሰላም በመውረዱ ኅብረተሰቡ ደስተኛ ነው፤” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ፣ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ፣ በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው ከነበሩ ከ475 ሺሕ በላይ ሰዎች መካከል፣ 430ሺሕ የሚኾኑቱ ወደየአካባቢያቸው መመለሳቸውንና ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ የመፈናቀል ኹኔታ እንደሌለ፣ የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

በተያያዘ፣ በጋምቤላ ክልልም፣ በጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) እና በመንግሥት መካከል፣ ባለፈው ሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ፣ በክልሉ ውስጥ ለውጦች መታየታቸውን፣ የጋነግ የቀድሞው ጦር መሪ ጋትሉዋክ ቡም ለቪኦኤ ተናግረዋል።

የክልሉ የጸጥታ እና ሰላም ግንባታ ቢሮ ምክትል ሓላፊ ኡቶው ኡኮት በበኩላቸው፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሰላም ስምምነቱ መፈረሙ፥ ክልሉን ከጸጥታ ስጋት ነፃ እንደሚያደርግ፣ ዜጎች ያለስጋት መንቀሳቀስ እንደሚችሉና ተበላሽተው የነበሩ ማኅበራዊ ትስስሮችን መልሶ ማጠናከር፣ ለሰላሙ መመለስ ወሳኝነት እንዳለው ለአሜሪካ ድምፅ አስረድተው ነበር።

በሁለቱም ክልሎች ውስጥ የነበሩ የትጥቅ ትግል አካሔዶች፣ ከዚኽ ቀደምም እንደነበሩ የሚያስረዱት፣ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር እና ቢዝነስ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጋትሉዋክ ሮን ናቸው። በግጭት እና አፈታቱ ዙሪያ በርካታ ጥናቶችን ማከናወናቸውን የሚናገሩት ዶር. ጋትሉዋክ፣ ስለ መንሥኤውም አብራርተዋል።

ሸማቂዎቹ፣ ከመንግሥት ጋራ የሰላም ስምምነት ፈርመው መመለሳቸው የሚበረታታ መኾኑን የጠቆሙት

ዶክተር ጋትሉዋክ፣ ሁለቱም አካላት የገቡትን ቃል መጠበቅ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ለዚኽም፣ በህወሓት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የተፈረመውን ስምምነት እና አተገባበር እንደ አርኣያነት ሊቀበሉት የሚገባ ነው፤ ሲሉ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲው ምሁር አስረድተዋል።

በሌላ በኩል፣ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል፣ በታንዛኒያ የራስ ገዝ አስተዳደር በኾነችው የዛንዚባር ደሴት የተጀመረው የቅድመ ድርድር ንግግር ላይም፣ “ሁለቱ አካላት ሰላም ለማውረድ ቢስማሙ የተሻለ ነው፤” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ከዚኽ ቀደም፣ ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋራ ግንኙነቱን ማቆሙን ያስታወቀው፣ የቀድሞ ጋነግ ሸማቂ ቡድንም፤ ታጣቂ ኃይሉ ወደ ሰላም ስምምነት እንዲመጣ ጥሪ ስለማቅረቡ መዘገባችን ይታወሳል።

በመንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተካሔደው የቅድመ ድርድር ንግግር፣ ባለፈው ሳምንት ውስጥ፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ ሳይደረስ መጠናቀቁ ተገልጿል።

XS
SM
MD
LG