በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ: የሰላም መንገዶች - አንድ ዓመት ከፕሪቶሪይያ ወዲህ


ኢትዮጵያ: የሰላም መንገዶች - ልዩ የቴሌቪዥን ውይይት
please wait

No media source currently available

0:00 0:58:41 0:00

ኢትዮጵያ: የሰላም መንገዶች - ልዩ የቴሌቪዥን ውይይት

የአሜሪካ ድምፅ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት፣ “ኢትዮጵያ: የሰላም መንገዶች - አንድ ዓመት ከፕሪቶሪይያ ወዲህ” በሚል ርእስ፣ የአንድ ሰዓት ተኩል ልዩ የቴሌቪዥን ውይይት ውይይት አዘጋጅቷል።

ውይይቱ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል፣ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ-ፕሪቶርያ ላይ የተፈረመው “ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነት” አፈጻጸም በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ከዘላቂ ሰላም፣ ከተጠያቂነት፣ ከዴሞክራሲ እና ከሰብአዊ መብቶች አያያዝስ አንጻር ምን ውጤት አመጣ? የሚሉትንና ሌሎችንም ጥያቄ ያነሣል።

በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ስቱድዮ በተካሔደው በዚኽ ውይይት፣ የተለያዩ ሐሳቦች ያሏቸው ትውልደ ኢትዮጵያን ተገኝተው ሐሳባቸውን አንሸራሽረዋል።

የስቱዲዮ ተወያይ እንግዶች የነበሩት፡-

የስቱዲዮ ተወያዮች
የስቱዲዮ ተወያዮች
  • አቶ ጌታቸው ተማረ፥ የሕግ ባለሞያ እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ናቸው።
  • መዓዛ መሐመድ፥ የሮሃ ቴቪ ተባባሪ መሥራች እና ዋና አዘጋጅ፣ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ናቸው። የአሜሪካ መንግሥት በየዓመቱ የሚሰጠው የዓለም አቀፍ ጽኑ ሴቶች ሽልማት የዘንድሮ ተሸላሚም ናቸው።
  • ዶክተር ኄኖክ ጋቢሳ፣ ዓለም አቀፍ ሕግንና ሰብአዊ መብቶችን ያጠኑ የሕግ ባለሞያ ናቸው። በዓለም አቀፍ የኦሮሞ የሕግ ባለሞያዎች ማኅበርም ተባባሪ ሊቀ መንበር ኾነው ያገለግላሉ።

በስካይፕ መሥመራችን ላይ የተገኙ ተወያዮች የነበሩት፡-

በስካይፕ መሥመራችን ላይ የተገኙ ተወያዮች የነበሩት
በስካይፕ መሥመራችን ላይ የተገኙ ተወያዮች የነበሩት
  • አቶ ሰዒድ ቦሩ፥ በኦሃዮ ግዛት ነዋሪ ናቸው። በአሜሪካ የሚኖሩ የአፋር ተወላጆች ማኅበር ሊቀ መንበርም ናቸው።
  • አቶ ኢሳይያስ ኀይለ ማርያም፥ የሕግ ባለሞያ ናቸው። “የፕሪቶርያ ስምምነት በተለይ ለትግራይ ሕዝብ ምን አመጣ?” በሚል የግምገማ ጹሑፍ አሳትመዋል።
  • አቶ ልደቱ አያሌው፥ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሰላማዊ ትግል ስልት ሳያሰልሱ በግንባር ቀደምነት በመሳተፍ ጉልሕ ተሳትፎ ያላቸው ታዋቂ ፖለቲከኛ ናቸው። በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምሥረታ እና አመራርነትም ይታወቃሉ። አኹን በዩናይትድ ስቴትስ፣ አትላንታ ግዛት ውስጥ ይኖራሉ።
  • ረዳት ፕሮፌሰር ጉባኤ ጉንዳርታ፥ በፍሎሪዳ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህር ናቸው።

ለተወያዮች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል፥ የሰላም ስምምነቱ፣ ለሁለት ዓመታት በአስከፊ ጦርነት ውስጥ ለቆየው የትግራይ ሕዝብ ምን አስገኘ? ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ በዐማራ ክልል በቀጠለው ግጭት የተለያዩ የመብቶች ጥሰቶች እንደተፈጸሙ ቀደም ብለው የወጡ በርካታ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ይህ ስምምነት በክልሉ ላይ፣ ስለምን ሰላምን ለማምጣት አልቻለም? የሚሉ ይገኙበታል።

ሌላው የውይይቱ ትኩረት፣ በከፍተኛ ኹኔታ አሳሳቢ እንደኾነ የሚገለጸው፣ በኦሮሚያ ክልል የሚካሔደው ግጭት ነው። መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚያደርጉትንም ግጭት በድርድር ለመፍታት፣ በታንዛኒያ የተጀመሩት ድርድሮች ያለስምምነት ቢጠናቀቁም እንዲቀጥሉ ግፊት እየተደረገ ነው። ይኹንና፣ ከፕሪቶርያው ልምድ በመነሣት፣ ስምምነት ላይ ቢደረስ እንኳ ራሱን ችሎ ብቻውን ለውጥ ማምጣት ይችላል? የሚለው ጥያቄም ለተወያዮች የቀረበ ነበር።

የሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰበት አካባቢ አንዱ የአፋር ክልል ነው። የሰላም ስምምነቱ በተለይ ከሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት እና የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ከመመለስ አንጻር በክልሉ ምን አምጥቷል? ምንስ ይቀራል? በፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ውስጥ የሕግ ክፍተቶች አሉ? የሚሉ ጥያቄዎችም ተነሥተዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት እና ከዚያ በፊት በነበሩ ዓመታት፣ በደቡባዊው የኢትዮጵያ ክፍል፥ ከዐዲስ ክልሎች አወቃቀር እና አደረጃጀት፣ ከአስተዳደራዊ ወሰንና የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎች ጋራ ተያይዘው በሚነሡ ግጭቶች የብዙዎች ሕይወት አልፏል። የሰሜኑ ጦርነት ደግሞ፣ እነዚኽ ግጭቶች ትኩረት እንዳያገኙ አድርጓቸው ነበር።

ከፕሪቶርያው ስምምነት በኋላስ፣ ግጭቶቹ የሚገባቸውን ትኩረት ለማግኘት ችለዋል? በአጠቃላይ የሰላም ስምምነቱ፥ በሰሜን ኢትዮጵያ በህወሓት እና በመንግሥት መካከል የነበረውን ጦርነት ያስቁም እንጂ፣ ግጭቶች አኹንም በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ቀጥለዋል። ለምንድን የፕሪቶርያው ስምምነት፣ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ያልቻለው? የሚሉ ጥያቄዎችም ለተወያዮች እይታ ቀርበዋል።

የስቱዲዮ እንግዶች
የስቱዲዮ እንግዶች

ተወያዮቹ፣ የፕሪቶርያ ስምምነት በዋናነት የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ማስቆም መቻሉ ትልቁ ፋይዳ እንደኾነ ገልጸው፣ የቀጠሉ ግጭቶችን ለማስቆም እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እንዳይችል ያደረጉትን ምክንያቶች አስረድተዋል። የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ማኅበረሰቦችን በእኩልነት ያሳተፉ ቅን ፖለቲካዊ ውይይቶችን ማካሔድ፣ ግጭቶቹን ለማስቆም መሠረታዊ ቅድመ ኹኔታ እንደኾነ አብራርተዋል።

መንግሥት፣ የሰላም ስምምነቱ አካል በኾነው የሽግግር ፍትሕ እና ሌሎች ሀገራዊ ምክክሮች፣ በአገሪቱ የቀጠሉትን ችግሮች በሒደት እንደሚፈታው ቢገልጽም፣ እነዚኽ ሒደቶች የተኣማኒነት ጥያቄዎች ይነሣባቸዋል። እውን ሒደቶቹ መፍትሔ ሊያስገኙ ይችላሉ? ካልኾነስ፣ በኹሉም ኅብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው፣ ኹሉንም ማኅበረሰብ የሚያስማማ ዘላቂ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው በምን መልኩ ነው? የሚሉ የመፍትሔ ሐሳቦችንም ተወያዮቹ አጋርተዋል።

በኢትዮጵያ ተፈላጊውን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት፣ በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሚና ምን ሊኾን ይገባል? በሚል፣ ከአድማጮች ለቀረቡ ጥያቄዎችም የበኩላቸውን ምላሾች ሰጥተዋል።

/ሙሉ ውይይቱን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ/

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG