ተስፋ ማርያም ዳርጌ፣ ኮምቦልቻ ተወልዶ፣ መቐለ ያደገ ወጣት ፊልም ሠሪ ነው፡፡ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ በኢኮኖሚክስ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ፣ በሥነ ጥበብ ሥራዎች ላይ የመሳተፍ ሙከራዎችን ያደርግ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ከዚያም፣ ይኸው የጥበብ ፍላጎቱ ከጊዜ ጋራ እያደገ፣ ወደ ፊልም ሥራው መግባት እንዳለበት ከውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡
በውስጡ የተካበተውን የፊልም ጥበብ ዝንባሌ፣ በትምህርት ለማጎልበት፣ ቪድዮግራፊ እና የፊልም ሥራ ጥበብ ተምሯል፡፡ ወደ ሞያው ከተቀላቀለ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው ወጣቱ ፊልም ሠሪ፣ እስከ አሁን ድረስ 13 አጫጭር ፊልሞችንና ዶክመንተሪዎችን ሠርቶ በተለያዩ መድረኮች ለእይታ አብቅቷል፡፡
አጫጭር ታሪኮችን መስማት እና ማንበብ ስለምወድ፣ አጫጭር ፊልሞችን ወደ መሥራት አዘነበልኹ፤ የሚለው ተስፋ ማርያም፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚያያቸውን ክፍተቶች በፊልም ለመግለጽ እንደሚጥር ይናገራል፡፡ በማኅበረሰቡ ዘንድ እጅጉን የተለመዱ ሥነ ቃሎችንና ባህሎችን ይዘት በመፈተሽ ላይ እንደሚያተኩርም ያመለክታል፡፡
በፊልም ሥራዎቹ ጥያቄ ማንሣትን ይወዳል፡፡ ፊልም፣ ለተመልካቹ መልዕክት የማስተላለፊያ መንገድ እንደኾነ ቢያምንም፣ “በሥራዎቼ፥ እንዲህ አድርግ ወይም አታድርግ አልልም፤ ሐሳብ ነው የምቆሰቁሰው፤ የመሰለኝን ሐሳብ ብቻ እናገራለኹ፤” ይላል፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በማተኮር በሠራቸው ፊልሞቹ፣ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ለማሸነፍ እንደበቃ ይናገራል፡፡ በቅርቡ፣ “መዳረሻዬ የት ነው?” የሚል፣ በወጣቶች ስደት ላይ የሠራው ፊልም፣ የአውሮፓ ኅብረትን ዓለም አቀፍ ሽልማት አሸንፏል፡፡
ስደት፣ ጠቃሚም ጎጂም ሊኾን ይችላል፤ የሚለው ተስፋ ማርያም፣ በዚኹ ፊልሙ፣ ወጣቶች ከመሰደዳቸው በፊት፣ ስለ መዳረሻቸውና ስለ መንገዳቸው ቆም ብለው እንዲያስቡ፣ የሚሰደዱበትን ዓላማ በግልጽ እንዲለዩ፣ እንዲሁም ከማን ጋራ እና በምን ኹኔታ እንደሚሰደዱ ቀድመው እንዲያውቁ የሚተርክ ፊልም እንደኾነ ያብራራል፡፡
ከዚህ ቀደምም እንዲሁ፣ በአውስትራሊያ በተካሔደ የፊልም ፌስቲቫል፣ “ታያለች” በሚል፣ በአካል ጉዳተኞች ችሎታ ላይ በሚያጠነጥን አጭር ፊልም ተወዳድሮ እንዳሸነፈ ይናገራል፡፡
ሙሉውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።