ይኽ ወር በአብዛኛው የአፍሪካ አካባቢ የወባ በሽታ የሚጀምርበት ወቅት ነው። በአህጉሩ ደግሞ እንደወባ በከፍተኛ ሁኔታ ገዳይ የሆነ በሽታ የለም፣ በተለይ ደግሞ ለሕፃናት። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር 90 ከመቶ የሚደርሰውን የአሜሪካ አለማቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤይድ) የውጭ ርዳታ ውሎች ለማቋረጥ መወሰኑ ታዲያ የወባ በሽታ ስርጭትን በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ከፍተኛ ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል የአህጉሩ የሕክምና ባለሞያዎች እያስጠነቀቁ ነው።
በሌላ በኩል፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዬ ዛሬ ሰኞ በኤክስ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፣ የትራምፕ አስተዳደር ላለፉት ስድስት ሳምንታት የዩኤስኤይድ አብዛኛውን ፕሮግራም የመዝጋት ሥራ ማጠናቀቁን እና ከመዘጋት የተረፈው 18 ከመቶ የርዳታ እና ልማት ፕሮግራም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስር እንደሚጠቃለል አስታውቀዋል።
ሩቢዮ በዛሬ የኤክስ መልዕክታቸው ዩኤስ ኤይድ ይመራቸው ከነበሩት 6ሺሕ 200 ፕሮግራሞች ውስጥ 5ሺሕ 200 የሚኾኑት መሰረዛቸውን አስታውቀዋል። "ፕሮግራሞቹ ለዩናይትድ ስቴትስን ብሔራዊ ጥቅም የማያገለግል (እንደውም አንዳንዴ የሚጎዳ) በቢሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ አባክኗል" ብለዋል። የትኞቹ ፕሮግራሞች እንደተረፉም ኾነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በምን መልኩ እንደሚያስቀጥላቸው ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም። በአሶስየትድ ፕረስ የተጠናቀረውን ዘገባ ስመኝሽ የቆየ ወደ አማርኛ መልሳዋለች።