በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“ኢ-መደበኛ ጥቃቶች ለሚዲያው ፈተና ኾነዋል” - መዓዛ መሐመድ


“ኢ-መደበኛ ጥቃቶች ለሚዲያው ፈተና ኾነዋል” - መዓዛ መሐመድ
please wait

No media source currently available

0:00 0:31:13 0:00

መዓዛ ሽልማቷን ለመቀበል እዚኽ ዩናይትድ ስቴትስ በመጣችበት ወቅት፣ ስመኝሽ የቆየ በአሜሪካ ድምፅ ስቱዲዮ ጋብዛ አነጋግራት ነበር። ዛሬ መዓዛን ስለ ሥራዋ እና የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛዎች አሁን ስላሉበት ኹኔታ የሰጠችውን አስተያየት፣ ዛሬ በመላው ዓለም በሚከበረው የፕሬስ ነፃነት ቀን አጋርተነዋል።

የሮሃ ቲቪ ተባባሪ መሥራች እና ዋና አዘጋጅ መዓዛ መሐመድ፥ በዩቲዩብ በሚሠራጨው ብዙኃን መገናኛዋ በምታስተላልፋቸው መረጃዎች ተደጋጋሚ እስር፣ ወከባ እና ዛቻዎች ቢደርሱባትም፣ በሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል በተካሔደውና ከስድስት ወራት በፊት በሰላም ስምምነት በተጠናቀቀው ጦርነት ለተጎዱ ሴቶች ድምፅ ኾና ለመቀጠል መወሰኗን ትገልጻለች።

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት፣ ከስድስት ወር በፊት የቆመው፣ ሁለቱ ወገኖች በደቡብ አፍሪካ በአካሔዱት የሰላም ንግግር ተኩስ ለማቆም ከተስማሙ በኋላ ነው። ከትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነቱ፣ ወደ ዐማራ እና አፋር ክልሎች ሲዛመት፣ መዓዛ ወደ አካባቢው በመሔድ፣ ታጣቂ ቡድኖች በሴቶች ላይ ያደረሱትን አስገድዶ መድፈር እና ሌሎችንም ፆታዊ ጥቃቶች ዘግባለች። ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች፣ ሕክምና እና ሌሎች ድጋፎችን እንዲያገኙም ሠርታለች።

መዓዛ፥ ብዙኃን መገናኛን በመጠቀም፣ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ለደረሱባቸው ሰዎች ድጋፍ በማድረግ እና ጥቃት አድራሾች ተጠያቂ እንዲኾኑ፣ ድምፅዋን በማሰማት ለአሳየችው ብቃት፣ ባለፈው ወር፣ ዩናይትድ ስቴትስ፥ በየዓመቱ አደጋን፣ ፍርሃትንና አስጨናቂ ኹኔታዎችን በቆራጥነት ተቋቁመው ሞያዊ ግዴታቸውን ለሚወጡ የአእምሮ እና የሞራል ጥቡዓን የምትሰጠውን የ“ብርቱ/ጥኑ ሴቶች”(Women of Courage) ሽልማት ተሸላሚ ኾና ነበር።

ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ በአደረገችው ቆይታ፣ “በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው ሴቶች እና ሕፃናት፣ ልክ እንደሌላው ማኅበረሰብ የሚደርስባቸው ችግር እንዳለ ኾኖ፣ በተጨማሪ ደግሞ ለፆታዊ ጥቃቶች ተጋላጭ ነበሩ፤” ያለችው መዓዛ፣ “በጦር ሜዳ ለሚመጣው ሽንፈት፣ ሴቶች የቂም በቀል መወጫ ይደረጉ ነበር። በዚያ ምክንያት፣ ዐያሌ ሴቶች ተደፍረው፣ ብዙዎቹ ለኤች.አይ.ቪ እና ለሌሎች የአባላዘር በሽታዎች ተጋልጠው አገኘኋቸው። ስለዚኽ ሙሉ ሐሳቤንና ትኩረቴን ያደረግኹት፣ እነርሱን በማገዝ ላይ ነው። ዓለም ጥቃታቸውን እንዲሰማላቸው በማድረግ ብቻ ሳይኾን፤ የሕክምና፣ የሥነ ልቡና ድጋፍ የሚያገኙበትን መንገድ ከተለያዩ ሰዎች ጋራ በመኾን ለመሥራት ወሰንኹ፤” ብላለች።

መዓዛ፣ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ዋይት ኃውስ ቤተ መንግሥት ለተካሔደው፣ 17ኛው ዓለም አቀፍ የ“ብርቱ ሴቶች” ሽልማት፣ ከልዩ ልዩ የዓለም ሀገራት ከተመረጡ 11 ሴቶች አንዷ ናት። መዓዛን ጨምሮ በብዙኃን መገናኛ ዘርፍ የተሸለሙትን ሦስት ሴቶች ያስተዋወቁት የዋይት ኃውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሪን ዣን ፒየር በአደረጉት ንግግር፣ “በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ዝም እንድትሉ በፈለጉበት ወቅት ለመናገር ጥብዓትን(አእምሯዊ እና ሞራላዊ ብርታት) ይጠይቃል፤” ብለዋል፡፡ “እነኚኽ ጋዜጠኞች፣ የቴሌቭዥን አዘጋጆች እና የጦርነት ዘጋቢዎች፥ እውነትንና ጽናትን ናኝተዋል፤ ሌሎች ሴቶች እና ልጃገረዶችም፥ ድምፃቸውን ለዴሞክራሲ፣ ለነፃነት እና ለፍትሕ እንዲጠቀሙ አበረታተዋል፤” ሲሉ አክለዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኝነት አዳጋች እና አደገኛ ሥራ ነው። ዛሬ የሚከበረውን የዓለም ፕሬስ ነፃነት ቀን አስመልክቶ፣ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት በአወጣው 180 ሀገራትን ያካተተ የዓለም ፕሬስ ነፃነት ዝርዝር መግለጫ፣ ኢትዮጵያ አምና ከነበራት 114ኛ ደረጃ አሽቆልቁላ ወደ 130ኛ ደረጃ ወርዳለች።

መቀመጫውን በፓሪስ ፈረንሳይ ያደረገው፣ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት፤ ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት ዙሪያ አስመዝግባው ከነበረችው እመርታ የኋሊት የተመለሰችው፣ “በጎሣ ግጭት እና በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በገባችበት ወቅት ነው፤” ሲል አስታውቋል።

መዓዛም ለአሜሪካ ድምፅ ስታስረዳ፣ “የኢትዮጵያ ሚዲያ፥ በአንድ ጊዜ ነው፥ ከነበረ ወደ አልነበረም እንዲዳከም የተደረገው፤” ትላለች።
“ሚዲያዎች መዘጋት ጀመሩ። የዩቲዩብ ቻናል ሳይቀር በብሮድካስት ባለሥልጣን ፈቃድ ቁጥጥር የሚደረግበት ኾነ። ኮሽ ባለ ቁጥር ኢንተርኔት ይዘጋል፤ ጋዜጠኞች ይታሰራሉ። አገሪቱ ላይ የኾነ ነገር ከተፈጠረ፥ እንደምንታሰር፣ ርምጃ እንደሚወሰድብን፣ ልንጠፋ እንደምንችል እናውቃለን።”


የብዙኃን መገናኛ ተቋማት ወደ ግጭቱ አካባቢ እንዳይደርሱ በተደረገው ክልከላ ምክንያት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሔደውን ጦርነት መዘገብ ከባድ ነበር፤ ሙከራ ያደረጉ ጋዜጠኞች፣ ለእንግልት ወይም ለእስር ተዳርገዋል። የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች የኾነው ሲፒጄ በአወጣው መረጃ መሠረት፣ ጦርነቱ እ.አ.አ በ2020 ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንሥቶ፣ ቢያንስ 60 ጋዜጠኞች በተለያዩ ጊዜያት ለእስር ተዳርገዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ፣ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ሞክረን አልተሳካልንም።

መዓዛ በዘገባዎቿ ትኩረት ያደረገችው፣ ጦርነቱ በተለይ በሴቶች እና በሕፃናት ላይ በአደረሰው ተጽእኖ ላይ ነው። በአንዳንድ የዐማራ እና የአፋር ክልሎች ተዘዋውራ፣ “በትግራይ ኃይሎች ጥቃት ደረሰብን፤” ያሉ ሴቶችን አነጋግራለች። ታጣቂዎቹ፣ በጦርነቱ የደረሰባቸውን ሽንፈት በቀል መወጫ እንዳደረጓቸውና በጠመንጃ አፈ ሙዝ ተደግኖባቸው እንደተደፈሩም በዘገባዋ አሳይታለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ባለፈው ዓመት በአደረገው ምርመራ፣ በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች፣ ፆታዊ ጥቃትን ጨምሮ ሌሎች አሠቃቂ ወንጀሎችን መፈጸማቸውን ይፋ አድርጓል። የትግራይ ኃይሎች ግን፣ በዐማራ እና በአፋር ክልሎች አስገድዶ የመድፈር እና ሌሎች ጥቃቶች ስለመፈጸማቸው የሚቀርብባቸውን ክሥ በማጣጣል ገለልተኛ የኾነ አካል እንዲያጣራ ጠይቀዋል።

መዓዛ፣ እ.አ.አ በ2019፣ በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኘው ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ በነበሩ የዐማራ ብሔር ተወላጅ ተማሪዎች ላይ በተፈጸመው እገታ ላይ ዘጋቢ ፊልም ሠርታለች። በወቅቱ የአሜሪካ ድምፅ ያናገራቸው የታገቱት ተማሪዎች ወላጆች፣ ልጆቻቸው በታጣቂዎች እንደተወሰዱባቸው አረጋግጠው ነበር።

መንግሥት፣ ተማሪዎቹ በሰላም ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚሠራ ግብረ ኃይል አቋቁሜያለኹ ብሎ የነበረ ቢኾንም፣ ተማሪዎቹ ግን እስከ አሁን ያሉበት እንደማይታወቅ፣ የመብት ተሟጋች ቡድን የኾነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል።

መዓዛ በእነዚኽ ሥራዎቿ ዓለም አቀፍ እውቅና ብታገኝም፣ ሥራዋን የሚቀበሉትና የሚደሰቱበት ግን ሁሉም አካላት አይደሉም። የኢትዮጵያ መንግሥት መዓዛን በተደጋጋሚ በማሰር፥ አሉባልታ በማሠራጨት፣ ከህወሓት ጋራ ግንኙነት እንዳላት በመጥቀስና በጦርነቱ ወቅት የብሔራዊውን ጦር መገኛ ቦታ በመጠቆም ወንጀሎች ክሥ አቅርቦባታል። በኢትዮጵያ የብሔር ወገንተኝነት ከፍተኛ ውጥረት በፈጠረበት ወቅትም፣ መዓዛ በአንድ ወገን “የዐማራ ደጋፊ” በሌላ ወገን ደግሞ “የህወሓት ደጋፊ” ናት የሚሉ ትችቶችን አስተናግዳለች። መዓዛ በበኩሏ፣ አብዛኛዎቹ ዘገባዎቿ በዐማራ እና በአፋር ክልሎች ላይ ያተኮሩት፣ በጦርነቱ ወቅት ልትደርስባቸው የቻለቻቸው አካባቢዎች በመኾናቸው ምክንያት መኾኑን ታስረዳለች።

መዓዛ፣ በኢንተርኔት ላይ ዘገባዎቿን የምታስተላልፍበት የዩቲዩብ ቻናል፣ ወደ 95ሺሕ የሚደርሱ ተከታዮች አሉት። የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች፣ በግጭቱ ውስጥ የሚሳተፉ የተለያዩ ወገኖች ቀጣይ የፍልሚያ መድረክም ኾነው ጥቅም ላይ እየዋሉ ቢኾንም፤ የብዙኃን መገናኛ ምኅዳሩ በየዕለቱ እየጠበበባት ባለችው ኢትዮጵያ፣ ለሚሊየኖች አማራጭ የመረጃ አውታር መኾኑንም ትገልጻለች።

“ባለፉት አምስት ዓመታት፣ ኢትዮጵያ ዕረፍት አልባ ኾናለች፤” የምትለው መዓዛ፣ “በተደራራቢ ችግሮች ውስጥ ነው ያለነው። በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ፣ ሰው የማይፈናቀልበት፣ የማይሞትበት ሰበብ የለም - በሃይማኖት፣ በታሪክ፣ በቋንቋ፣…ወዘተ.። በዚኽ የተመሳቀለ ኹኔታ ውስጥ ያለ ማኅበረሰብ፣ ማኅበራዊ ሚዲያውን እንዴት ይጠቀማል? ከባድ ነው። ይህ የሚስተካከለው ግን በመዝጋት አይደለም። የሚስተካከለው፥ ማኅበራዊ ንቃት በመፍጠር ነው፤” ስትል ሐሳቧን ለአሜሪካ ድምፅ አጋርታለች።

መዓዛ፣ በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተሰጣት ሽልማት፣ በጦርነቱ ወቅት ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች እንግልት እና ሥቃይ አጉልቶ ለማሰማት ሰፊ መድረክ እንዳስገኘላት ትገልጻለች። የብዙኃን መገናኛ ተቋሜን ተጠቅሜ፣ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ተጠያቂነት እና ፍትሕ እንዲሰፍን ፊት ማድረጌን እቀጥላለኹ፤ ስትል፣ የ2023 ዓለም አቀፍ “ብርቱ ሴቶች” ተሸላሚዋ መዓዛ ተናግራለች፡፡

XS
SM
MD
LG