በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩኤስ-አፍሪካ ጉባዔ የአሜሪካ-አፍሪካ ተጀመረ


የዩኤስ-አፍሪካ ጉባዔ የመጀመሪያ ቀን ውሎ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:21 0:00

የዩኤስ-አፍሪካ ጉባዔ የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ትላንት ሐሙስ በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የዩናይትድ ስቴትስና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሊ ጋር ተወያይተዋል።

በሌላ በኩል ትናንት የተጀመረው የዩኤስ-አፍሪካ ጉባኤ በያዛቸው አጀንዳዎች ላይ ሲነጋገር ውሏል። የአየር ንብርት ለውጥን ስለመቋቋም፣ ሰላም ፀጥታና አስተዳደር ከተወያየባቸው ጉዳዮች ጥቂቶቹ ናቸው። የአፍሪካ ወጣቶችንና የዳያስፖራን ሚና በተመልከተም በልዩ መድረክ ላይ ውይይት ተደርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከብሊንከን ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን በምታደርገው ጥረት ዩናይትድ ስቴትስ ላደረገችው አስተዋፅኦ አድናቆታቸውን መግለፃቸውን አመልክተው "አጋርነታችንን ለማጠናከር በሚቻልበት መንገዶች ዙሪያ ተወያይተናል" ብለዋል።

ጉባኤው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከጀመረ ወዲይ በዋሽንግተን ዲሲ የተካሄደ ትልቁ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ነው። ብሊንከን፣ የመከላከያ ኃላፊው ሎይድ ኦስትንና ሌሎች ቁልፍ የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች ከአፍሪካ መሪዎች ጋር በተናጠል እየተገናኙ የተነጋገሩ ሲሆን በተለያዩ የዲፕሎማሲ እና የፀጥታ የውይይት መድረኮች ላይም ተሳትፈዋል።

ከውይይቱ በኋላ ብሊንከን ባወጡት መግለጫ፤ ባለፈው ወር የተፈጸመው የሰላም ስምምነት ሂደት እድገት እያሳየ መሆኑንና ይህም በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን ቁልፍ እንደሆነ አውስተዋል። የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም የሰብዓዊ አቅርቦት በመሻሻሉና የመሰረታዊ አገልግሎቶች በመመለሳቸው የኢትዮጵያ መንግሥትን አድንቀዋል። በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች የኤርትራ ኃይል ኪትዮጵያ የሚወጣበትንና ይህም ከትግራይ ኃይሎች መሳሪያ መፍታት ጋራ በአንድ ላይ የሚከናወን እንደሆነ መነጋገራቸውን መግለጫው አውስቷል።

ባለፉት ጥቂት አመታት አሜሪካ ለአህጉሪቱ ባላት ቁርጠኝነት ዙሪያ ቁጣ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ዋይት ሀውስ ከአፍሪካ ጋራ ያለውን ጉልህ የመተማመን ልዩነት ለማጥበብ በሚፈልግበት በዚህ ወቅት፣ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በደርዘን የሚቆጠሩ የአፍሪካ መሪዎችን እያስተናገዱ ነው።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ ትኩረት ከሚደረግባቸው የመወያያ አጀንዳዎች መካከል ኮሮናቫይረስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያካሄደው ወረራ በአፍሪካ ላይ ያሳደረው ተፅእኖ፣ ንግድ እና ሌሎችም ይገኙበታል።

ብሊንከን እና ኦስትን ማክሰኞ ዕለት ከጅቡቲ፣ ኒጀር እና ሶማሊያ ፕሬዝዳንቶች ጋርም የተገናኙ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የነዳጅ ሀብቷ ከፍተኛ በሆነ የቻይና መዋዕለ ንዋይ የሚደገፈው እና ቻይና የባህር ኃይል ሰፈር እንድትከፍት ከፈቀደችው አንጎላ ፕሬዝዳንት ጋርም ተወያይተዋል።

ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ጋር ውይይት የተደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማክሰኞ እለት ባወጣው ሪፖርት አብዛኛው የሶማሊያ አካባቢ ለረሀብ መጋለጡን ባመለከተበት ወቅት ነው።

የመሪዎቹ ጉባኤ ከመጀመሩ በፊት፣ የአፍሪካ ኅብረት የቡድን 20 ቋሚ አባል እንዲሆን ባይደን እንደሚደግፉ ና በአህጉሪቱ የአስርት አመታት ልምድ ያካበቱትን አንጋፋ ዲፕሎማት ጆን ካርሰን ጉዳዩን እንዲከታተሉ እና ተግባራዊ እንዲያደርጉ መሾማቸውን ዋይት ኃውስ አስታውቋል።

ጉባዔው ከመጠናቀቁ በፊት ባይደን በሚቀጥለው አመት በአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት ጉብኝት እንደሚያደርጉ ያሳውቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አንድ ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣን ለአሶስዬትድ ፕሬስ ተናግረዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የተጋበዝዙት የአፍሪካ አገራት ፕሬዝደንቶችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ነበር በጉባኤው ላይ ለመታደም ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ያቀኑት።

የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ ‘በአፍሪካ እና ዳያስፖራ ወጣት መሪዎች መድረክ’ ላይ በመሳተፍ ነበር ቀናቸውን የጀመሩት።

“የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ፈጠራና ብልህነት የወደፊት ዓለማችንን ለመቀየር ይረዳናል የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ። ሃሳቦቻቸው፣ ሃሳቦቻችሁ፣ ፈጠራዎቻችሁና ተነሳሽነታችሁ ዓለምን ሁሉ የሚጠቅም ነው። የወጣቶች ቆራጥነት እኛን ወደፊት የሚወስደን መሆኑን ስለምንረዳ፣ የባይደንና ሃሪስ አስተዳደር ከእናንተጋ ለምቆም ይሻል” ብለዋል ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ።

አስተዳደራቸው ለ’ወጣት የአፍሪካ መሪዎች ተነሳሽነት’ ለተሰኘው ፕሮግራም ተጨማሪ 100 ሚሊዮን ዶላር መመደቡንና ለዩኤስ አስመጪና ላኪ ባንክ ደግሞ በአፍሪካ ንግድን ለመደገፍ 1 ቢሊዮን ዶላር የመግባቢያ ስምምነት ላይ እንደተደረሰ ምክትል ፕሬዝደንቷ አስታውቀዋል።

የዩናይትድ ስቴትሱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ከመከላከያ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስትን እንዲሁም ከአሜሪካ ዓለም ዓቀፍ ልማት ድርጅት (ዩኤሴኤይድ) ሃላፊ ሳማንታ ፓወር ጋር በመሆን ከኒጀር፣ ሞዛምቢክና ሶማሊያ ፕሬዝደንቶች እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኩ ማሃማት ጋራ በሰላም፣ አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ በአንድ መድረክ ላይ ተወያይተዋል።

“ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት አንድ ሞዴል ብቻ አይደለም ያለው። እርስ በእርሳችን ሃሳብ መቀያየር አለብን። እንደየአካባቢው ሁኔት መረጃዎችን ማግኘት አለብን። የአንድን አካባቢን ፍላጎት መረዳት አለብን፤ እንደ አሜሪካ ከሆነ ይህ ከሌሎች ጋር የሚደረግ ፉክክር አይደለም። ጓዶቻችንንና አጋሮቻችንን አንዱን መምረጥ አለባችሁ እያልን አይደለም። እውነተኛ አማራጭ ለማቅረብና እውነተኛ አጋርነትን ለመፍጠር ነው ሃሳባችን፤ እናም ተስፋችን ወደ ከፍታው አብረን መገስገስ ነው” ብለዋል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ባደረጉት ንግግር።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስት በበኩላቸው በጸጥታ ጉዳዮች ላይ አተኩረዋል።

“ለእናንተ አስፈላጊው ነገር ምንድን ነው? የሚለውን ለመረዳት እንፈልጋለን። እናንተን በሚጠቅም መንገድ የፀጥታ ሃይላችሁን ለማሳደግ፣ ለማስታጠቅና ብቁ ለማድረግ፣ እንዲሁም ቀጠናዊ መረጋጋትን ለመፍጠር መሥራት እንፈልጋለን” ብለዋል ሎይድ።

የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት አሜሪካ ለኒጀር፣ ሞዛምቢክ፣ ሶማሊያና ቻድ እርዳታ እንደምታደርግ ተናግረው፣ የአፍሪካ ሰራዊቶች በበቂ ያልታጠቁ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

“የችግሩን አሳሳቢነት በተመለከተ የአፍሪካን ጩኽት የሚሰማ የለም” ሲሉ ተናግረዋል ማሃማት።

የኒጀር ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ሞሃመድ ባዙም በበኩላቸው ዲሞክራሲንና ተያያዥ ምብቶችን ማጠናከር ዋናው ጉዳይ ነው ብለዋል።

“ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ተግባራትን በአንድ ላይ ማምጣት አለብን። የመጀመሪያው ዲሞክራሲን፣ የህግ የበላይነትን እና ሰብዓዊ መብትን ማጠናከር ነው” ሲሉ ተናግረዋል ሞሃመድ ባዙም።

ጉባኤው በዛሬው ሁለተኛ ቀኑ ውሎው በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ የአፍሪካን ሚና ለማሳደግና ቁልፍ የሆኑ ዘርፎችን ለማጠናከር፣ የሁለትዮሽ ንግድ እና መዋዕለ ነዋይን በተመለከተ በሚደረግ ትብብር ላይ ያተኩራል ተብሎ ይጠበቃል።

XS
SM
MD
LG