በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከብሊንከን ጋር ተወያዩ


ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከብሊንከን ጋር ተወያዩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:00:18 0:00

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ትላንት በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ እና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ተወያይተዋል። ውይይቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን በምታደርገው ጥረት ዩናይትድ ስቴትስ ላደረገችው አስተዋፅኦ አድናቆታቸውን ገልፀው "አጋርነታችንን ለማጠናከር በሚቻልበት መንገዶች ዙሪያ ተወያይተናል" ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ትላንት ሐሙስ በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ እና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሊ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን በምታደርገው ጥረት ዩናይትድ ስቴትስ ላደረገችው አስተዋፅኦ አድናቆታቸውን መግለፃቸውን አመልክተው "አጋርነታችንን ለማጠናከር በሚቻልበት መንገዶች ዙሪያ ተወያይተናል" ብለዋል።

ጉባኤው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከጀመረ ወዲይ በዋሽንግተን ዲሲ የተካሄደ ትልቁ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ነው።

ብሊንከን፣ የመከላከያ ኃላፊው ሎይድ ኦስቲንና ሌሎች ቁልፍ የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች ከአፍሪካ መሪዎች ጋር በተናጠል እየተገናኙ እየተነጋገሩ ሲሆን በተለያዩ የዲፕሎማሲ እና የፀጥታ የውይይት መድረኮች ላይም ተሳትፈዋል።

ባለፉት ጥቂት አመታት አሜሪካ ለአህጉሪቱ ባላት ቁርጠኝነት ዙሪያ ቁጣ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ዋይት ሀውስ ከአፍሪካ ጋር ያለውን ጉልህ የመተማመን ልዩነት ለማጥበብ በሚፈልግበት በዚህ ወቅት፣ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በደርዘን የሚቆጠሩ የአፍሪካ መሪዎችን እያስተናገዱ ነው።


ለሦስት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ ትኩረት ከሚደረግባቸው የመወያያ አጀንዳዎች መካከል ኮሮናቫይረስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያካሄደው ወረራ በአፍሪካ ላይ ያሳደረው ተፅእኖ፣ ንግድ እና ሌሎችም ይገኙበታል።


ብሊንከን እና ኦስቲን ማክሰኞ እለት ከጅቡቲ፣ ኒጀር እና ሶማሊያ ፕሬዝዳንቶች ጋርም የተገናኙ ሲሆን ከቅርብ አመታት ወዲህ የነዳጅ ሀብቷ ከፍተኛ በሆነ የቻይና መዋዕለ ንዋይ የሚደገፈው እና ቻይና የባህር ኃይል ሰፈር እንድትከፍት ከፈቀደችው አንጎላ ፕሬዝዳንት ጋርም ተወያይተዋል።


ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ጋር ውይይት የተደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማክሰኞ እለት ባወጣው ሪፖርት አብዛኛው የሶማሊያ አካባቢ ለረሀብ መጋለጡን ባመለከተበት ወቅት ነው።

የመሪዎቹ ጉባኤ ከመጀመሩ በፊት፣ የአፍሪካ ህብረት የቡድን 20 ቋሚ አባል እንዲሆን ባይደን እንደሚደግፉ እና በአህጉሪቱ የአስርት አመታት ልምድ ያካበቱትን አንጋፋ ዲፕሎማት ጆን ካርሰን ጉዳዩን እንዲከታተሉ እና ተግባራዊ እንዲያደርጉ መሾማቸውን ዋይት ኃውስ አስታውቋል።

ጉባዔው ከመጠናቀቁ በፊት ባይደን በሚቀጥለው አመት በአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት ጉብኝት እንደሚያደርጉ ያሳውቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አንድ ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣን ለአሶስዬትድ ፕሬስ ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG