በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቻይና በዩናይትድስቴትስ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ማጥላቷ ተዘገበ


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንተኒ ብሊንከን ዋሽንግተን በሚካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ እና አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉ - Dec. 12, 2022.
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንተኒ ብሊንከን ዋሽንግተን በሚካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ እና አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉ - Dec. 12, 2022.

በርከት ያሉ የአፍሪካ መሪዎች ወደ ዋሽንግተን ባቀኑበት በያዝነው ሳምንት የባይደን አስተዳደር የአህጉሪቱን ኢኮኖሚ በተመለከተ ከቻይና ጋር በያዘው ውድድር ለአፍሪካ አጋሮቹ ግልፅ እና የተሻለ አማራጭ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

ለሦስት ቀናት የሚቆየው እና ዛሬ የጀመረው የዩናይድ ስቴትስ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ከመከፈቱ አስቀድሞ ቻይና ዩናይድ ስቴትስ በአፍሪካ የምታፈሰውን የቀጥታ መዋዕለ ንዋይ መጠን በማለፏ አገራቸው ወደ ኋላ ቀርታለች ያሉት ምክትል የንግድ ሚንስትር ዶን ግሬቭስ ፤ ይሁን እንጂ ዩናይትድ ስቴትስ “ተመራጯ አጋር” ነች ሲሉ ተከራክረዋል።

“እንደሚባለው ዓይናችንን ከኳሷ ላይ በመንቀላችን” አሉ ምክትል ሚንስትሩ “ዓይናችንን ከኳሷ ላይ በመንቀላችን አሁን የዩናይትድ ስቴትስ ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች ያመለጣችውን ደርሰው ለመያዝ ብዙ መፍጠን ሊኖርባቸው ነው።” ብለዋል። አክለውም "ምርጥ ቴክኖሎጂዎችን እና ፈጠራዎችን፣ እንዲሁም የላቁ ደረጃዎችን እያመጣን ነው።.... ዩናይትድ ስቴትስ አጋሮቻችንን መበዝበዝ ሳይሆን አቅማቸውን ለመገንባት በያዙት ጥረት ትረዳለች።" ነበር ያሉት።

የ49 የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች እና የአፍሪካ ህብረት የተጋበዙበት ይህ ጉባኤ ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ከአህጉሪቱ መሪዎች ጋር ለመስራት የሚያስችል ሁለተኛ እድል ሆኖ ነው የተሰናዳው።

የምጣኔ ሃብታቸውን ለማልማት በቂ እድል እንዳልተሰጣቸው የሚሰማቸው የአህጉሪቱ ሃገራት መሪዎች በፍጥነት እያደገ በመጣው የህዝባቸው ቁጥር፣ ባላቸው እምቅ የተፈጥሮ ሃብት እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ከሚኖራቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ድምጽ አንጻር በዓለም ወሳኝ ኃይል ሆነው መቀጠላቸው አይቀሬ ነው።

በተመሳሳይም የባይደን አስተዳደር ዋናዋ የዩናይትድ ስቴትስ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ተፎካካሪ አድርጎ በሚለከታት ቻይና ላይ ልዩ ትኩረት የሚያደርገውን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ፖሊሲ በአዲስ መልክ ለማጠናከር አፍሪካ እጅግ ግዙፍ ስትራቴጂካዊ እና ጠቀሚ አህጉር ሆና ትቀጥላለች።

ለዚህም ጉባኤው በይፋ ከመጀመሩ በፊት የአፍሪካ ሕብረት “ቡድን 20” በመባል የሚታወቀው ስብስብ ቋሚ አባል ትሆን ዘንድ ዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ እንደምትሰጥ ዋይት ሃውስ አስታውቋል። ውጥኑን ለማሳካትም በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸውን አንጋፋውን ዲፕሎማት ጆኒ ካርሰንን የጉዳዩ ተከታታይ ዋና ሰው አድርጎ መሰየሙን ይፋ አድርጓል።

የዋይት ሃውስ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ትላንት ሰኞ ሲናገሩ፣ የባይደን አስተዳደር በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ “በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ያሉትን የዘመናችንን ቁልፍ ፈተናዎች ለመቅረፍ” 55 ቢሊዮን ዶላር ለአፍሪካ ይመድባል” ብለዋል።

ሱሊቫን አክለውም “ዩናይትድ ስቴትስ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ልታከናውን ቀደችውን ሌላ ማንኛውን ሃገር ሊያደርግ ካቀደው ጋር ብታነፃፅሩ እጅግ የተለየ ግምት ትሰጡታላችሁ” ብለዋል።

የባይደን አስተዳደር ቻይና በአህጉሪቱ ያላት የተንሰራፋ እንቅስቃሴ፣ በዚህ ሳምንት ለሚደረገው ጉባዔ ዋና ምክንያት ነው የሚለውን ስጋት ለማቃለል ቢሞክርም ወረርሽኙ ከጀመረበት ከሶስት አመት ወዲህ ለመጀመሪያ ግዜ በዋሽንግተን ላይ በሚካሄደው ትልቁ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የቤይጂንግ ጉዳይ ማጥላቱ አልቀረም።

የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል የግምጃ ቤት ኃላፊ ዋሊ አዴዬሞ በትላንትናው ዕለት በሰጡት አስተያየት ቻይናን በቀጥታ ሳይጠቅሱ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች በተለይም አፍሪካ ውስጥ የግል ኢንቨስትመንት በዝግታ እያሽቆለቆለ ነው ሲሉ የማስጠንቀቂያ ድምጽ አሰምተዋል።

ለመሠረተ ልማት የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን፣ ለመኖሪያ ቤቶች እና ለንግድ ድርጅቶች የሚቀርበው የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኮቪድ ወረርሽኝ ያሳደረውን ተጽዕኖም ሆነ የከፋ የአየር ንብረት ማህበረሰቦች ላይ የደቀነው ፈተና ለመቋቋም የሚያግዙ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገው ገንዘብ በዓመት ከ68 ቢሊዮን እስከ 108 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ አዴዬሞ ተናግረዋል።

በተመሳሳይም በዓለም ዙሪያ ባሉ ባለጸጋ አገሮች ውስጥ ያለው ከፍተኛ መጠን ያለው የግል ካፒታል እስካሁን ገና አልተሠራበትም” ሲሉ ምክትል ኃላፊው ተችተዋል።

በሌላ ዜና የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ቻይና በምዕራባዊ የአፍሪካ የባህር ጠረፍ አካባቢ የጦር ሰፈር ለመገንባት አላት ያሉት ፍላጎት ያሳደረባቸውን ስጋት ገልጸዋል።

XS
SM
MD
LG