ኮዲንግ ማለት የሰዎችን ሀሳብ የሚገልፁ ትዕዛዛትን ኮምፒውተር ሊረዳው በሚችለው ቋንቋ መፃፍ ማለት ሲሆን ይህ ሂደቱ የሰዎችን የማሰብ፣ የመፍጠር እና እራስን የመግለፅ ችሎታ በእጅጉ ያሳድጋል።
አዲስ አበባ በሚገኘው ልደታ ካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ሳሙኤል ወራሽ ወላጆቹ ከህፃንነቱ ጀምሮ እንዲነካካ በፈቀዱለት ኮምፒውተር ምክንያት የቴክኖሎጂ ፍቅሩ እንዳደገ ይገልፃል።
ሳሙኤል ስቴም ሲነርጂ ተቋም በኮዲንግ እና ሮቦቲክ ለስድስት ወር አሰልጥኖ ካስመረቃቸው ጥቂት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አንዱ ነው። ሳሙኤል ለመመረቂያው ከጓደኛው ናሆም ሰለሞን ጋር በመሆን የኤ ቲ ኤም ማሽን የሰራ ሲሆን በአጭር ግዜ የሰሩት ስራ በርካቶችን አስገርሟል።
የ18 አመቱ ናሆምም ልክ እንደ ሳሙኤል ለቴክኖሎጂ ቅርብ ሆኖ ነው ያደገው። በካቴድራል ትምህርት ቤት ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን የሚጀምረው ናሆም ለመጀመሪያ ግዜ የኮዲንግ ስልጠና የወሰደው ገና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ነው።
ወደፊት አይሮስፔስ ማጥናት የሚመኘው ናሆም የኮዲንግ ትምህርት ከልጅነት መሰጠቱ ተማሪዎች የተሻለ እውቀት ይዘው እንዲያድጉ እና ወደፊት የበለጠ ፈጣሪ እንዲሆኑ ያስችላል ብሎ ያምናል።
ልጇ ከህፃንነቱ ጀምሮ ኮምፒውተር የመነካካት ፍቅር እንደነበረው የምታስታውሰው የሳሙኤል እናት ወይዘሮ የሱነሽ ተሾመም ልጇ ተሰጥኦውን እንዲያዳብር ታግዘው እንደነበር ትገልፃለች።
በልጇ ውጤት እጅግ የተደሰተችው የሱነሽ ሌሎች ወላጆች እና ተቋማት ተማሪዎች በስይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች እንዲያበረታቱ ማድረግ አለባቸው ትላለች።
ህፃናት ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ኮዲንግን እንዲማሩ በትምህርት ስርዓቷ ውስጥ እንዲካተት በማድረግ ኬንያ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር ሆናለች።
በኢትዮጵያም ተማሪዎች የኮዲንግ እና ሮቦቲክ ስልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ ከሚንቀሳቀሱ የትምህርት ተቋማት አንዱ የሆነው ስቴም ሲነርጂ አሰልጥኖ ያስመረቃቸው እነዚህ ተማሪዎች ከኮዲንግ በተጨማሪ በርካታ ክህሎቶችንም ይዘው እንደሚመረቁ የተቋሙ የቦርድ አባል አቶ ፀጋዬ ለገሰ ያስረዳሉ።
ስቴም ሲነርጂ በመጀመሪያ ዙር ያስመረቃቸው ተማሪዎች ከኤ ቲ ኤም ማሽን በተጨማሪ የትራፊክ መብራት እና የፓርኪንግ ስርዓትን የሚቆጣጠሩ ቴክኖሎጂዎችን ሰርተዋል።
ይህ አይነቱ ክህሎት ወደፊት ስራ በማጣት የሚቸገሩ ወጣቶችን ቁጥር ከመቀነስ ባሻገር አዳዲስ ይስራ ዘርፎችን ለመፍጠር እንደሚያስችል የሚገልፁት አቶ ፀጋዬ፣ ተቋማቸው የኮዲንግ ትምህርት በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ተካቶ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ዩንቨርስቲዎች ድረስ እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንዲሰጥ ለማድረግ ጥረት መጀመሩን ይገልፃሉ።
ሳሙኤል እና ናሆም የሰሩት የኤ ቲ ኤም ማሽን ወደፊት ለሚያስቡት የሙያ ዘርፍ መነሻቸው ነው። ስሙኤል ሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ተምሮ ናሆም ደግሞ ኤይሮስፔስ አጥንቶ ሀገራዊ ችግሮችን መቅረፍ የሚችሉ የፈጠራ ስራዎችን መስራት ህልማቸው ነው።