የአሜሪካ እንደራሴዎች የኦሮምያ ጉዳይ ሪፖርት እንዲቀርብላቸው ጠየቁ

  • ቪኦኤ ዜና

የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት ሕንፃ ጉልላት

የዩናይትድ ስቴትስ አራት የሕዝብ እንደራሴዎች ለሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃን ኬሪ በጋራ ደብዳቤ ፅፈው ኢትዮጵያ ኦሮምያ ክልል ውስጥ ስለተፈጠረው ሁኔታ በዘጠና ቀናት ውስጥ ዝርዝር ማብራራያ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ አራት የሕዝብ እንደራሴዎች ለሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃን ኬሪ በጋራ ደብዳቤ ፅፈው ኢትዮጵያ ኦሮምያ ክልል ውስጥ ስለተፈጠረው ሁኔታ በዘጠና ቀናት ውስጥ ዝርዝር ማብራራያ እንዲሰጧቸው ጠየቁ።

የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ አባላት ጄፍሬ መርክሌ እና ራን ዋይደን፤ እንዲሁም የሕግ መምሪያው አባላት ኧርል ብላሚኖር እና ሱዛን ባናሚቺ፤ ዓርብ፣ መጋቢት 9/2008 ዓ.ም ፈርመው ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በላኩት ደብዳቤ ላይ ኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ጠቃሚ አጋርና ከውጭ እርዳታዋም ግንባር ቀደም ተቀባዮች አንዷ መሆኗን አመልክተዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ እንደራሴዎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃን ኬሪ ስለኦሮምያ ሪፖርት እንዲያቀርቡላቸው የጠየቁበት ደብዳቤ

ይሁን እንጂ መንግሥታቸው የሚሰጠው ገንዘብ የዩናይትድ ስቴትስን ዘላቂ ጥቅሞችና እሴቶቿን የሚጎዱ አለመሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ እንደራሴዎቹ አሳስበዋል።

በመሆኑም በመጭዎቹ ዘጠና ቀናት ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኦሮምያ ክልል ውስጥ ለተነሣው ተቃውሞ የሃገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች በሰጡት ምላሽ በሰው ላይ የደረሱ ጉዳቶችን፣ የዘፈቀደ እሥራቶችን፣ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎችን ዝርዝር እንዲያቀርቡላቸው እንደራሴዎቹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል።

ከተቻለም ለተፈፀሙት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጠያቂ ነው የሚባል ሰው ወይም ሰዎችን ማንነት እንዲለዩና በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ወንጀሎችን የፈፀሙ ሰዎችን ሕግ ፊት ለማቅረብ መንግሥቱ የወሰዳቸው እርምጃዎች ካሉም እንዲያሳውቋቸው እንደራሴዎቹ አክለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አሳስበዋል።