ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዩናይትድ ስቴትስና አፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ለመካፈል ዋሽንግተን ዲሲ ለሚገኙ የአፍሪካ መሪዎች ትላንት ማታ የዕራት ግብዣ አድርገውላቸዋል። ከተወሰኑ የአፍሪካ መሪዎች ጋራ በተናጠል በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የተመረጡትን የአፍሪካ ሀገሮችን ዝርዝርም ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትላንት በዋሽንግተን ለተሰበሰቡት የአፍሪካ መሪዎች በዋይት ኃውስ ባደረጉት የዕራት ግብዣ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ "ለአፍሪካ መጪ ዘመን በሙሉ አቅሟ ትሰራለች" ሲሉ ተናግረዋል። በጤና፣ በመሰረተ ልማት፣ በቢዝነስ እና በቴክኖሎጂ እያደገች ያለችውን አህጉር ለማገዝ አሜሪካ በቢሊየን የሚቆጠር የመንግስት ገንዘብ እና የግል መዋዕለ ንዋይ መመደቧንም አብራርተዋል።
ፕሬዚዳንቱ አፍሪካንና አሜሪካን ለዘላለም የሚያስተሳስራቸውን ግንኙነት አስመልክተው ሲናገሩም "ሕዝባችን የሚኖረው አሜሪካንና አፍሪካን ለዘላለም በሚያስተሳስረው ረቂቅ እና ጥልቅ ትስስር መካከል ነው። በሰንሰለት ታስረው በባህር ዳርቻዎቻችን በኩል እንዲገቡ የተደረጉትንና ለማይታሰብ ጭካኔ የተዳረጉትን ወንዶች እና ሴቶች እናስታውሳለን።” ብለዋል።
አክለውም “የሀገሬ የመጀመሪያ ሀጢያት ያ ዘመን ነበር። ይህችን ሀገር በመገንባትና ከፍ እንድትል በማድረግ፣ በኃላፊነት በመምራት፣ አዳዲስ መንገዶችን የፈነጠቁ እና በአሜሪካ ውስጥ ላለ ሁሉም ሰው የተሻለ የወደፊት ህይወት የፈጠሩ የሆኑትን የነሱን ትውልዶች እናከብራለን።" ሲሉ ተናግረዋል።
ጆ ባይደን ለተናጥል ስብሰባ የተመረጡ የአፍሪካ መሪዎችን ስም ዝርዝር ይፋ አድርገዋል
ጆ ባይደን ለተናጥል ስብሰባ የተመረጡ የአፍሪካ መሪዎችን ስም ዝርዝር ይፋ አድርገዋልአፍሪካውያን አሜሪካን እንደ ሀገር ዛሬ ያለችበት ደረጃ ለማድረስ የከፈሉትን መስዋዕትነት ከማንሳት ባሻገር ዛሬ በአሜሪካ የሚኖረው የአፍሪካ ማህበረሰብም እንዲሁ ለአሜሪካ ዕድገት ያለውን አስተዋፅኦ ባይደን አንስተዋል። በመጀመሪያው ጥቁር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ማገልገላቸውንም አፅንኦት ሰጥተው አስታውሰዋል።
"ዛሬ በአሜሪካ የሚኖረውን የአፍሪካ ዳያስፖራ ማህበረሰብም እናከብራለን። በአሜሪካ ያሉ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ጠንካራ ህዝቦች እንደ አንድ በጥብቅ የተሳሰረ ቤተሰብ እንኖራለን። እዚህ ላይ የቀድሞ አለቃዬ የነበሩትን እና ከሳቸው ጎን ሆኜ ለስምንት ዓመታት በማገልገሌ ክብር እንዲሰማኝ ያደረገኝን ሥራ ላንሳ፡፡ ባራክ ኦባማን እና እሳቸው ፕሬዝዳንት እያሉ ስላስተናገድነው የመጀመሪያው የዩናይትድ ስቴትስ እና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ለማንሳት እፈልጋለሁ። እንደ መሪ ህዝባችን ያበረታታናል። በእጃችን ውስጥ ያሉ ዕድሎች እንድናይ ይቀሰቅሰናል። አብረን ከሰራን ብዙ የሚቻሉ ነገሮች አሉ። ለመስማት የሚከብዱንን እውነቶች ይነግሩናል። የዚች ሀገር መስራቾች ያስቀመጡልንን እሴቶች ጠብቀን እንድንኖር እና ለተሰጠን የተቀደሰ አደራ ኃላፊነታችንን በብቃት እንድንወጣ ይፈትኑናል"፡፡ ብለዋል፡፡
ባይደን አክለው አብሮ መስራት በተለይ ለመጪው ትውልድ የተሻለ ነገር ለማውረስ ያለውን ጥቅም አስምረውበታል።"ለዓመታት በፖለቲካ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ እንዳሳለፈ ሰው እንደአሁን የተስፋ ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም። ከልቤ ነው የምናገረው፣ ስለወደፊቱ የጋራ ዕጣችን ከዚህ በላይ በተስፋ ተሞልቼ አላውቅም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ህዝባችን፣ በተለይ ደግሞ የየሀገሮቻችን ወጣቶች ናቸው። በጋራ ጤናማ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ የበለጠ እኩል፣ የበለጠ ፍትሃዊ፣ የበለጠ የበለፀገ እና ለሁሉም ሰው የበለጠ ዕድል የተሞላበት ዓለም ዕውን ማድረግ እንችላለን” ብለዋል።
ባይደን በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ በዋይት ኃውስ የተሰበሰቡት መሪዎች እና ተጋባዦች ለአዲስ ትብብር ያላቸውን መልካም ምኞት ፅዋቸውን በማንሳት እንዲገልፁ ጋብዘዋል።"ለአሜሪካ ህዝብ፣ ለዩናይትድ ስቴትስ፣ ለአፍሪካ ህዝብ እና ወደፊት ለሚኖረን አጋርነት ለተገባው ቃል እባካችሁ ፅዋችሁን ወደላይ ከፍ አድርጉ! "የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳልም እንዲሁ አፍሪካ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ለሚኖራት ትብብር ተጋባዦች ፅዋቸውን እንዲያነሱ ጠይቀዋል።
"ለአስተናጋጃችን ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ለቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን ክብር፣ ለአሜሪካ ህዝብ ክብር እና በአሜሪካ እና አፍሪካውያን መካከል ልለው ትብብር መጠናከር በአፍሪካ ስም ሁላችሁም ፅዋችሁን እንድታነሱ እጠይቃለሁ!!”።
በዋይት ኃውስ ከተካሄደው የራት ግብዣ በተጨማሪ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በጉባዔው ላይ ለተገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የእራት ግብዣ አድርገዋል።
ብሊንከን በግብዣው ላይ ባደረጉት ንግግር “አጋርነት የፕሬዝዳንት ባይደን የአፍሪካ ስትራቴጂ እምብርት ነው” ያሉ ሲሆን “በተለይ በዓለም ላይ የተደቀኑትን የአየር ንብረት ለውጥ፣ ንፁህ ታዳሽ ኃይል፣ የህብረተሰብ ጤና፣ ኢኮኖሚ፣ የሰላም እና የፀጥታ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ችግሮች ለመፍታት የተሻለው እና ውጤታማው መንገድ የንግዱን ማህበረሰብ ጥረት ጨምሮ የተቀናጀ ትብብር ማድረግ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎችን ለማራመድ እና ወሳኝ የጤና እና የኃይል እድገትን ወደፊት ለመግፋት አሜሪካ ታማኝ አጋር መሆኗን አስረግጠው እየገለፁ ያሉት ባይደን በሚቀጥሉት ሶስት ዐመታት 55 ቢሊየን ዶላር የሚገመት መዋዕለ ንዋይ በአፍሪካ እንደምታፈስ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ አስታውቀዋል። ከ15 ቢሊየን ዶላር በላይ ደግሞ በግል ንግድ እና መዋዕለ ንዋይ ትብብሮች ቃል መገባቱን አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በጉባዔው ለአፍሪካ መሪዎች ባደረጉት ጉባኤ ዩናይትድ ስቴትስ ከአዲሱ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ሴክሬታሪያት ጋር ታሪካዊ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟን እና ይሄም ከዚህ በፊት ያልታየ ሲሉ የገለጹትን ከቀረጥ ነፃ ዕድል እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
በተጨማሪም ሚሊኒየም ቻሌንጅ ኮርፖሬሽን የተሰኘው የአሜሪካ የውጭ ርዳታ ተቋም ለመጀመሪያ ግዜ በአፍሪካ መንገዶችን ለመገንባት፣ የትራንስፖርት ወጪን ለመቀነስ እና በተለይ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በፍጥነት ምርቶቻቸውን ለማጓጓዝ የሚያስችላቸው የ 500 ሚሊየን ዶላር ስምምነት ከአፍሪካ መንግስታት ጋር መፈራረሙንም ይፋ አድርገዋል።
አሜሪካ ዲሞክራሲን ለማጠናከር ከአፍሪካ ህብረት ጋር እንደምትሰራ የገለፁት ባይደን “መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ የሚፈልጉ የአሜሪካ የንግድ ተቋማት ወደ አፍሪካ እንዲሄዱ ወይም የአፍሪካ ኢኮኖሚ ወደፊት እንዲሻገር የመልካም አስተዳደር፣ የጤናማ ማህበረሰብ እና የተመጣጣኝ የኃይል አቅርቦት መኖር ወሳኝ ነው” ብለዋል።ለሶስት ቀን በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ባለው የዩናይትድ ስቴትስ እና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ፕሬዚደንት ባይደን ከተመረጡ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋር የተናጠል ስብሰባ የሚያደርጉ ሲሆን እነርሱም ጋቦን፣ ናይጄሪያ፣ ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ማዳጋስካር እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሆናቸውን ትላንት ይፋ አድርገዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ፣ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በኃያላን ሀገራት መካከል ለሚደረገው ፉክክር ቁልፍ የጦር ሜዳ በሆኑት ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ከቻይና ወደ ኃላ ቀርታለች። አፍሪካ በፍጥነት እያደገ በሚሄደው የህዝቧ ቁጥር በግዙፍ የተፈጥሮ ሃብቷ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትልቅ ድምፅ ሰጪ ቡድን ያላት በመሆኗ በዓለም ኃይል አሰላለፍ ቁልፍ ሚና አላት። በመሆኑም የባይደን አስተዳደር በውጪ ፖሊሲው ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ባላንጣ አድርጎ የሚመለከታትን ቻይናን ትኩረቱ ባደረገበት በዚህ ወቅት አፍሪካ ለዩናይትድ ስቴትስ ትልቅ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላት አህጉር መሆኗን ትቀጥላለች።