የትግራይ ክልልን የሰላም ግንባታ እና መልሶ ማቋቋም አዳጋች የሚያደርግ፣ ከባድ የረኀብ አደጋ እያንዣበበ እንደሆነ ያመለከቱት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፣ ለትግራይ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ የድጋፍ ጥሪ አቅርበዋል።
“የሰላም ግንባታ እና ፍትሕ በድኅረ ጦርነት ትግራይ” በሚል ርእስ፣ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ በድረ ገጽ በተካሔደው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ አቶ ጌታቸው ሲናገሩ፣ ሕዝቡን ከረኀብ አደጋ ለመታደግና በጦርነቱ የወደመውን መንግሥታዊ መዋቅር ወደነበረበት ለመመለስ የዳያስፖራ ማኅበረሰቡ ሚና አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሌላው የኮንፈረንሱ ተናጋሪ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣ ከባድ የረኀብ አደጋ እንደሚኖር በአቶ ጌታቸው የተገለጸውን ከፍተኛ ስጋት እንደሚጋሩ ጠቅሰው፣ ከብዙ አጋሮቻችንና ለጋሾች ጋራ በትብብር መሥራታችን እንቀጥላለን፤ ብለዋል። በስርቆት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የምግብ ርዳታ ማከፋፈል፣ አሁን በአጥጋቢ ሁኔታ መግባባት ስለተደረሰበት ምግብ ማከፋፈሉ ተጀምሯል፤ ሲሉም አክለዋል፡፡
“ለሰላም፣ ፍትሕ እና ተጠያቂነት አስፈላጊ ሐሳቦችን ለማሰባሰብ” ታልሞ እንደተዘጋጀ በተገለጸው በዚኹ ዓለም አቀፍ የድረ ገጽ ኮንፈረንስ፣ በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም እስከ አሁን የታየው ፍጥነት “አላረካንም” ሲሉ መጓተቱን ማይክ ሐመር አመልክተዋል፡፡ “የኤርትራ ኀይሎች ሙሉ በሙሉ ከትግራይ
ክልል የሚወጡበትን ቀን እየጠበቅን ነው፤” ያሉት ልዩ መልዕክተኛው፣ ለተጠያቂነት መረጋገጥም “ቁርጠኞች ነን” ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት ለመፍታት ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸው፣ በአማራ ክልልም በፌደራል መንግሥቱ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ድርድር እንዲካሔድ ለመገፋፋት “ፍላጎታችን ነው፤” ብለዋል። ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ከተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ጋራ በተያያዘ፣ ከሶማሊያ ጋራ የተፈጠረውን መካረር ያነሡት ሐመር፣ ሁሉም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ቀጣናው ሊሸከመው የማይችለውን ሌላ ግጭት እንዲያስወግዱ ጥሪ አቅርበዋል።
የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ 14 ወራት እንደተቆጠሩ ያወሱት ጌታቸው ረዳ ደግሞ፣ የተፈናቀለው ሕዝብ ወደ ቀዬው ሳይመለስና ሕገ መንግሥታዊ የትግራይ ክልል ግዛታዊ አንድነት ሳይረጋገጥ፣ ሰላሙ መሠረት ሊኖረው እንደማይችል አሳስበዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አያይዘው እንዳመለከቱት፣ ሰላሙ የተሟላ ሊሆን የሚችለው ደግሞ፣ በፌደራል መንግሥቱ በተገለጸው የሽግግር ፍትሕ ሒደት፣ ዓለም አቀፍ የፍትሕ አካላት የተካተቱበትና የትግራይ ክልል የተሳተፈበት ተጠያቂነት ሲረጋገጥ ነው፡፡
ዘገባውን ያጠናቀረው የትግርኛ ክፍል ባልደረባ ገብረ ገብረ መድኅን ነው፤ ሀብታሙ ሥዩም በድምጽ አቅርቦታል።