በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በረሃብ የሞቱ አሉ ወይስ የሉም? ቃኝዎችና መንግሥት


በረሃብ የሞቱ አሉ ወይስ የሉም? ቃኝዎችና መንግሥት
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:15 0:00

በረሃብ የሞቱ አሉ ወይስ የሉም? ቃኝዎችና መንግሥት

በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ክልሎች ድርቅ ባስከተለው ረሃብ ተጎድተው የሞቱ ሰዎች እንዳሉ የየአካባቢው ባለሥልጣናትና ተጎጂዎች እየተናገሩ ቢቆዩም ፌደራል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ሺፈራው ተክለማርያም ግን ድርቅ መኖሩን ገልፀው ጉዳቱ “ወደ ረሃብነት ደረጃ አልደረሰም” ብለዋል።

ኮሚሽነሩ ለሃገር ውስጥ የብዙኃን መገናኛ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ድርቅ በተከሠተባቸው አካባቢዎች መንግሥት ሁኔታውን እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅሩ መፈተሹን ተናግረዋል።

ወደ ረሃብነት ደረጃ አልደረሰም”

ኮሚሽነሩ እንዲያውም “’ረሃብ ገብቷል’ የሚሉ ከሣይንሳዊ መሠረት ይልቅ ሌላ ዓላማ ሊኖራቸው ይችላል” ብለዋል። ያ “ዓላማ” ያሉት ምን እንደሆነ ግን አላብራሩም።

ይሁን እንጂ ድርቅ በተከሠተባቸው የሰሜን ጎንደርና የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች እንዲሁም የትግራይ ክልል ምሥራቃዊ ዞንና የአበርገሌ ወረዳ አካባቢዎች ባለሥልጣናትና የድርቅ ተጎጂዎች መሆናቸውን የሚናገሩ “በረሃብ ምክንያት ሰዎች መሞታቸውን” ቀደም ሲል በጥናት አስደግፈው አሳይተዋል።

ድርቅ በተከሠተባቸው ጠለምት፣ በየዳና ጃን አሞራ ወረዳዎች 37 ቀበሌዎች ውስጥ ከረሃብ ጋራ በተያያዘ 36 ሰዎች መሞታቸውን የሚጠቁም የጥናት ሪፖርት ሰሜን ጎንደር ዞን ውስጥ የሚገኘው ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የዛሬ ወር አካባቢ ይፋ አድርጎ ነበር።

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የድርቅ ጥናት ሰብሳቢ ረዳት ፕሮፌሰር አምሳሉ አበጀ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል በረሃብ ምክንያት የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ሰዉ በድርቁ ምክንያት ከየቤቱ እየተፈናቀለ መሆኑንም የወረዳዎቹ ባለሥልጣናትና ተጎጂዎቹ አመልክተዋል።

የዓዲ አርቃይ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ባለሞያ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ጌቴ አዛናው ድርቅ ከተከሠተባቸው ጠለምትና አጎራባች ወረዳዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ዓዲ አርቃይ ከተማ መግባታቸውን ገልፀዋል።

የስድስት ልጆች እናት መሆኗንና ከጠለምት ወረዳ ደጃች ሜዳ ቀበሌ መፈናቀሏን የምትናገረው ማርታ ክበበው እርሷና ልጆቿ ከሌሎች ተፈናቃዮች ጋር ከተማዩቱ ጎዳናዎች ላይ በአስከፊ ሁኔታ እየተንገላቱ መሆናቸውን ትናገራለች።

ጃን አሞራ ወረዳ የአስነጋ ቀበሌ ጤና ጣቢያ ኃላፊ መሆናቸውን የገለፁልን አቶ ይልማ ገብሬ ቀበሌያቸው ውስጥ በረሃብ ምክንያት የሞቱና የተፈናቀሉ እንዳሉ ተናግረዋል።

በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ ደጃች ሜዳ ቀበሌ ይኖሩ እንደነበር የገለፁት ወ/ሮ ሙሉ ኃይሌ ድርቁ ባስከተለው ረሃብ ምክንያት ዘጠኝ ልጆቻቸውን ይዘው ከአራት ቀናት የእግር ጉዞ በኋላ ዓዲ አርቃይ እንደደረሱ አመልክተዋል። በነበሩበት አካባቢ፣ የቅርብ ቤተሰባቸውን ጨምሮ ሰዎች በረኀብ ምክንያት መሞታቸውን እንደሚያውቁና ቀዬአቸውን ትተው ለመፈናቀል የገፋቸውም ይሄው እንደሆነ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ፣ በትግራይ ክልል ምሥራቃዊ ዞን አፅቢ እና አበርገሌ ወረዳዎች ውስጥ በረኀብ ምክንያት 157 ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት በቅርቡ ተናግረዋል። ከክልሉ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፅህፈት ቤት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

‘በረሃብ ምክንያት ሞተ’ ሊባል የሚችለው ምን ሲሆን ነው?

ለመሆኑ ሰው ‘በረሃብ ምክንያት ሞተ’ ሊባል የሚችለው ምን ሲሆን ነው? በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምግብና የሥነ ምግብ ማዕከል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር አሻግሬ ዘውዱ ሲመልሱ ሰዎች በረኀብ ለመሞት የሚያልፏቸው ሦስት ሂደቶች እንዳሉ ገልፀው በረሃቡ ምክንያት ሰውነት መርዛማ ኬሚካል እንደሚያመርትና ለኅልፈት እንደሚዳርግ አስረድተዋል፡፡

የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቋቋም መንግሥት 11 ቢሊዮን ብር እንደመደበ የገለፁት የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ሺፈራው ተክለማርያም በትግራይና በአፋር ክልሎች ሦስት ዞኖች፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ስምንት ዞኖች ውስጥ ለተራዘመ ጊዜ አለመዝነቡን ጠቅሰው እርዳታ ለማድረስ የሚደረጉ ጥረቶች በፀጥታ ችግር እንደሚስተጓጎሉ አመልክተዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG