ዚካ (ZIKA) የተባለው ትንኝ ወለዱ ቫይረስ በላቲን አሜሪካ ሀገሮች ጎልቶ መከሰት፥ መንግሥታቱን አስደንግጧል፥ በትንኙ ዘር ላይ ጦርነት እንዲያውጁ አስገድዷል።
የዚካ(ZIKA) ቫይረስ ወረርሺኝ የተከሰተው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ዘንድሮ ብራዚል በምታስተናግደው የኦሊምፒክ ውድድር ላይ ለመገኘት እየተዘጋጁባሉበት ወቅት ነው።
ፍራቸው በዓለምአቀፉ ውድድር ወቅት ቫይረሱን በዓለም ዙሪያ ለማሠራጨት ብራዚል ዋና ምክንያት ልትሆን ትችላለች የሚል ነው።
የብራዚል ፕሬዘዳንት ዲልማ ሮሰፍ (Dilma Rousseff) በትላንት ማታ ንግግራቸው፥ብራዚልያውያን በሙሉ፥ ዚካ (ZIKA)ን በሚያሠራጨው ትንኝ ላይ በሚካሄደው ውጊያእንዲተባበሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ሕዝቡ ትንኙን ለመከላከልና ለማጥፋት የሚያስችለውን መሣሪያና ወጪ ሁሉ የፌዴራሉ መንግሥት ለማቅረብ መዘጋጀቱን አረጋግጣለሁ ሲሉም ፕሬዘዳንቷ ቃል ገብተዋል።
በዘመቻው የሃገሪቱ የጦር ኃይል ባልደረቦችና፥ የመንግሥታቸው ባለሥልጣናት በሙሉ እንደሚሳተፉበትም አስረድተዋል።
የዓለም አቀፍ ወረርሽነት ጉባዔ
ዚካ በመባል በሚታወቀው ቫይረስ አማካኝነት በላቲን አሜሪካ አገሮች የአያሌ ሕጻናትን ህይወት ለአደጋ የዳረገው ሕመም በዓለም አቀፍ ወረርሽነት ይፈረጅ የሚለውን ለማጤን ተመራማሪዎችና የሕክምና ባለሥልጣናት የተገኙበት፤ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የጠራው ጉባዔ ተከፈተ።
በሕጻናት የነርቭ ሥርዓትን የሚያውክ ጉዳት በማስከተል የታወቀው ይህ ቫይረስ በያዝነው ዓመት ብቻ በሽታው በይበልጥ በተስፋፋባቸው የላቲን አሜሪካ አገሮች ቁጥሩ እስከ 4 ሚልዮን ሊደርስ እንደሚችል የተገመተ ሕዝብ ሊያጠቃ እንደሚችል ተተንብይዋል።
በቫይረሱና ማይክሮሴፋሊ (microcephaly) በመባል በሚታወቀው የነርቭ ስርዓት መዛባት በሚያስከትለው፥ ሕጻናት ከተለመደው ተፈጥሮ ውጭ አነስተኛ ጭንቅላት ይዘው በሚወለዱበት የሕመም ሁኔታ መካከል ያለውን ቁርኝት የሚያረጋግጠው ጥናትሙሉ በሙሉ ያለመቋጨቱ ቢታወቅም፤ በቅርቡ በብራዚል የተከሰተውን የመሰለ ቁጥራቸው የበዙ ሕጻናት ለህመሙ የተዳረጉበትን ሁነት ግን ቸል ማለትአይቻልም።
ካለፈው የጥቅምት ወር አንስቶ ብቻ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ለቫይረሱ መጋለጣቸው ተረጋግጧል። ይህም አሃዝ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2014ዓም(ከአንድ ዓመት በፊት በተመሳሳይ ጊዜ)150 ሰዎች ብቻ መታየታቸውንከተዘገበበት ጋር ሲነጻጸር በብዙ እጥፍ የላቀ ነው።