በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዚካ የዓመቱ የዓለም ሥጋት


ብራዚል በዚህ ካለፈው ግንቦት አንስቶ እያስጨነቃት ባለውና አሁን ከቁጥጥር ውጭ የሆነ በሚመስለው ዚካ ቫይረስ ተቀስፈው ከተያዙት የላቲን አሜሪካ ሃገሮች አንዷ ነች።

ግዙፏ የብራዚል ከተማ ሪዮ ዴ ጃኔይሮ የፊታችን ነኀሴ ውስጥ 31ኛውን ኦሊምፒያድ ታስተናግዳለች።

ከዓለም ዙሪያም በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተወዳዳሪነትም፣ በቡድን አባልነትም፣ በደጋፊነትም በሺሆች እና በሺሆች የሚቆጠሩ የሰው ዘር ልጆች ይጎርፉባታል ጨዋታዎቹ የሚካሄዱት ከሐምሌ 28 ወይም 29 እስከ ነኀሴ 15 ቢሆንም ከዚያ ቀደም ሲልም በዝግጅቱ ወቅት ወጣ ገባ የሚል አይጠፋም።

ብራዚል በዚህ ካለፈው ግንቦት አንስቶ እያስጨነቃት ባለውና አሁን ከቁጥጥር ውጭ የሆነ በሚመስለው ዚካ ቫይረስ ተቀስፈው ከተያዙት የላቲን አሜሪካ ሃገሮች አንዷ ነች። በመሆኑም ሪዮ የዚካ ሥርጭት ማዕከል እንዳትሆንም በብዙ እየተፈራ ነው። የብራዚል ፕሬዚዳንት ዲልማ ሩሴፍ ጦርነቱን ዛሬውኑ አውጀዋል፡፡ ጦርነቱ የሚካሄደው ቤት ለቤትና ከደጅ ደጅ ነው።

ለብሄራዊ ዘመቻው ሲቪሉን ሕዝባቸውን ብቻ ሳይሆን ጠራቸውንም እንደሚያንቀሣቅሱ ፕሬዚዳንት ሩሴፍ ለሃገራቸው የኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ለዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴና ለኮሚቴው የጤናና የሳይሣዊ ኮሚሽን ቃል ገብተዋል፡፡ ዚካን የምታስተላልፈው መደበኛዋ የወባ አስተላላፊ ቢምቢ ናት።

ይህ መካከለኛውንና ደቡቡን አሜሪካ ያጥለቀለቀው ዚካ ቫይረስ ዛሬ እንዲህ ገነነ እንጂ መጀመሪያም መኖሩ የታወቀው የዛሬ ሰባ ዓመት (በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በ1939 እና አርባ ዓ.ም አካባቢ መሆኑ ነው) ስሙን ባገኘበት በዩጋንዳው ዚካ ጫካ ነበር፡፡ ቢምቢ ዋነኛዋ ተሸካሚ ትሁን እንጂ ዚካ ከነፍሰጡር ወደ ፅንስም ሊተላለፍ የመቻሉ ነገር ሥጋቱን አበርትቶታል።

አሁን ብራዚል ውስጥ በዚካ የተያዘው ሰው ቁጥር ከአንድ ሚሊየን በላይ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህ ቁጥር ወደ ሦስት እና አራት ሚሊየን ሊያድግ እንደሚችል ተተንብይዋል፡፡ ቫይረሱ ብራዚል ውስጥ እያደረሰ ያለው ጉዳት ጁሊያን-ቤር ሲንድረም እየተባለ የሚጠራውን የጡንቻ መላሸቅ እና እንዲያውም የመላ ሰውነት አለመታዘዝን ቁጥር እንዳበረከተው የዓለም የሕክምና ማኅበር ሰሞኑን አሳውቋል።

በነፍሰጡር እናቶች እና በፅንሳቸው ወይም በአራስ ልጆቻቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሰው የነርቭ ችግር ፈጣሪው ዚካ ሕፃናቱ ከቀሪ የሰውነታቸው ክፍል ጋር ተመጣጣኝ ያልሆኑ ትናንሽ ራሶች ኖረዋቸውና የአዕምሮ ወይም የአንጎልም ጉዳት ደርሶባቸው እንደሆነ ተረጋግጧል።

ለመሆኑ ከኦሊምፒክ መንደር የማትጠፋው፤ እንዲያውም ብዙ ጊዜ ጎላ ብለው ከሚታዩት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ስለዚህ ጉዳይ ምን እያደረገች ይሆን? የጤናና የስፖርት ባለሥልጣናቱን ምላሽ ወደፊት ይዘንላችሁ እንመለሳለን፤ ለዛሬ ግን ለተጨማሪ ዘገባ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ዚካ የዓመቱ የዓለም ሥጋት
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:35 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG