ዚካ የተባለው በሚወልዱ ህጻናት ላይ የአካል ጉድለት ያስከትላል የሚባለው ቫይረስ በመላ የአሜሪካ ሀገሮች በፍጥነት እየተዛመተ በመሆኑ አራት ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎችን ሊያጠቃ ይችላል ሲል የዓለም የጤና ድርጅት አስጠንቅቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅቱ የጤና አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ ማርግሬት ቻን በትንኝ የሚተላለፈው ዚካ ቫይረስ እአአ በ 1947 ዓ.ም. ለመጀምርያ ጊዜ የተገኘው ኡጋንዳ ውስት እንዳነበር ገልጸዋል። ከዚያ በኋላ በመላ አለም ተስፋድቷል።
ከቅርብ ጊዝያት ወዲህ ደግሞ ከአካላት ነርቮች ጋር እየታያያዘ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል። በሽታው የያዛቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ነፍሰ-ጡር ሴቶች ከፍተኛ የአካል ጉዳት ያለባቸው ልጆች ወልደዋል ብለዋል። እንደተወለዱ የሞቱ ህጻናትም እንዳሉ አክለውበታል።
“በአሁኑ ወቅት 23 የአሜሪካ ሀገሮችና ግዛቶች በሽታው እንደታየባቸው ቻን ገልጸዋል። የቫይረሱ መግባት በጣም ትንሽ ጭንቅላት ያላቸው ህጻናት መወለድ መብዛት ጋር ተያይዟል” ሲሉም ማርግሬት ቻን አስረድተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕረዚዳንት ባራክ ኦባማ የዚካ በሽታ ምርመራ፣ ክትባትና ህክምና ለማቅረብ ፈጣን ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።