በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአለም ጤና ድርጅት ግርዛት ለተፈፀመባቸው በሚልዮን ለሚቆጠሩ አለም አቀፍ ሴቶችን ለመንከባከብ አዲስ መመሪያ አወጣ


የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ከ200 ሚልዮን ለሚበልጡ በህፃንነታቸው ግርዛት ለደረሰባቸው ሴቶች የአካልና የስነአዕምሮ እንክብካቤ እንዴት ሊደረግላቸው እንደሚገባ ለመጀመሪያ ጊዜ መመሪያ አወጣ።

የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት እንደዘገበው በየአመቱ እድሜያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑ ወደ ሶስት ሚልዮን የሚጠጉ ልጃገረዶችና ሴቶች ያለፍላጎታቸው ግርዛት ተፈፅሞባቸዋል። ይህ ቁጥርም ከነበሩት ጋር ሲደመር ከሁለት መቶ ሚልዮን በላይ ልጃገረዶችና ሴቶች የድርጊቱ ሰለባዎች ሆነዋል።

የሴት ልጅ ግርዛት በ30 የአፍሪካ ሃገሮች፣ በእስያና በመካከለኛው ምስራቅ በስፋት እየተተገበረ ይገኛል። ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው ፍልሰተኛና ስደተኛ ምክንያትም በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካም በግርዛት የተጎዱ ልጃገረዶችና ሴቶች ቁጥር ተበራክቷል።

የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) የማኅበረሰብ የስነልቦና ጤና ምርምር አስተባባሪ ሌል ሴይ (Lale Say) የሴት ልጅ ግርዛት የሚያስከትለው ህመምና ከፍተኛ የደም መፍሰስ ችግር እስከሞት እንደሚያደርስ አስረግጠው ተናግረዋል።

የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት እንዳስታወቀው የጤና ባለሙያዎች የሴት ልጅ ግርዛት የደረሰባቸውን ልጃገረዶችና ሴቶች እንዴት መንከባከብ እንዳለባቸው በትክክል አልተረዱም ነበር። የጤና ተቋማቱ ውሳኔ ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የማህፀን ችግሮችን ማከምና መከላከል እንዲሁም በአእምሮ ጭንቀትና ድብታ የታወኩ ሴቶችን መርዳትን ይጨምራል። መመሪያው በተጨማሪም የሴቶች ግርዛትን ከህክምና ጋር የተያያዘ ማድረግን ያስጠነቅቃል።

እንደ አለም አቀፉ የጤና ድርጅት አዲሱ መመሪያ በስፋት የሚተገበረውን የሴት ልጅ ግርዛት ለማስቆም፣ ምን ያህል ጎጂ ድርጊት እንደሆነና ከግርዛቱ ጋር በተያያዘ የሚደርሰው የጤና ችግር በግልፅና በስፋት ለማስተማር ይረዳል።

የአሜሪካ ድምጽ ባልደረባችን ሊሳ ሽላይን (Lisa Schlen) ጄኔቫ ከሚገኘው የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት የላከችውን ዘገባ መስታወት አራጋው አቅርባዋለች። ከበታች ያለውን የድምፅ ፋይል በመጫን ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ።

ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG