በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“ረሃቡ በትምህርት ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው” የትግራይ ክልል የት/ቢሮ


“ረሃቡ በትምህርት ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው” የትግራይ ክልል የት/ቢሮ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:05 0:00

“ረሃቡ በትምህርት ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው” የትግራይ ክልል የት/ቢሮ

በትግራይ ክልል በረሃብ ምክንያት 223 ሺሕ የሚሆኑ ተማሪዎች “ትምህርታቸውን ከማቋረጥ ቋፍ ላይ ናቸው” ሲል የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለፀ::

“የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሩን በመጀመር ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ማድረግ ይገባል” ሲልም አሳስቧል::

በክልሉ ኢሮብ ወረዳ በጦርነቱ እና በድርቁ ከ3600 በላይ ተማሪዎች እንዲሁም በአፅቢ ወረዳ አስር ሺሕ የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን የአካባቢው አመራሮች ገልጸዋል::


የተባበሩት መንግሥታት ዕርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (UN-OCHA) ትናንት ባወጣው ሪፖርት በበኩሉ በክልሉ 105 ትምህርት ቤቶች በተፈናቃዮች መጠለያነት መያዛቸውን ገልጿል::


በኢሮብ ወረዳ በአከባቢው የተፈጠረው ድርቅ ባስከተለው ረሃብ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ እያስገደደ መሆኑን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ኢያሱ ተስፋይ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል::

“በወረዳው ካሉ 47 ትምህርት ቤቶች ሃያ አራቱ በኤርትራ ኅይሎች በተያዙ አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው” ያሉት አቶ ኢያሱ “በዚህ ዐመት መመዝገብ ይገባቸው የነበሩ ተማሪዎች ከ7600 በላይ ሲሆን የተመዘገቡት ግን 4101 ብቻ ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በረሃብ እና ተያያዥ ጉዳዮች በዚህ ወረዳ 63 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉንም አስተዳዳሪው ተናግረዋል::

በአፅቢ ወረዳ የውቕሮ ደራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ሚዛን ኪዳኑ “በረሃብ የተነሳ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እየቀሩ ነው” ብለዋል::

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኅላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዕሽ ጦርነቱ በትምህርት ስርዓቱ ላይ ከፈጠረው ከፍተኛ ተፅዕኖ በተጨማሪም ድርቁ እና ረሃቡ በትምህርት ሥርዐቱ ላይ ትልቅ ጫና አሳድሯል ብለዋል:: በትግራይ ክልል ድርቅ በተከሰተባቸው 36 ወረዳዎች 223 ሺሕ ገደማ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማቋረጥ አፋፍ ላይ ናቸው ሲሉ ኅላፊው አስረድተዋል::

ለተማሪዎች ምገባ እስከ ሰኔ ወር ድረስ የ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ዶክተር ኪሮስ ተናግረዋል::

የተባበሩት መንግሥታት ዕርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (UN-OCHA) ትናንት ባወጣው ሪፖርት “በክልሉ 105 ትምህርት ቤቶች ተፈናቃዮች እየተጠለሉባቸው በመሆኑ ትምህርት ቤቶቹን ለመክፈት የሚደረገው ጥረት እየተደናቀፈ ነው” ብሏል:: ህፃናት ይበልጡን ለችግር እንዲጋለጡ ማድረጉንም አመልክቷል፡፡

በትግራይ እና አማራ ክልሎች ከድርቅ እና ከምግብ እጥረት ተያይዞ የሚከተለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመከላከል ሁለተናዊ ድጋፍ በአስቸኳይ እንደሚያስፈልግ የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮው አሳስቧል::


ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ያገኛሉ፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG