በትግራይ ክልል በረሃብ ምክንያት 223 ሺሕ የሚሆኑ ተማሪዎች “ትምህርታቸውን ከማቋረጥ ቋፍ ላይ ናቸው” ሲል የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለፀ::
“የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሩን በመጀመር ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ማድረግ ይገባል” ሲልም አሳስቧል::
በክልሉ ኢሮብ ወረዳ በጦርነቱ እና በድርቁ ከ3600 በላይ ተማሪዎች እንዲሁም በአፅቢ ወረዳ አስር ሺሕ የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን የአካባቢው አመራሮች ገልጸዋል::
የተባበሩት መንግሥታት ዕርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (UN ኦቻ) ትናንት ባወጣው ሪፖርት በበኩሉ በክልሉ 105 ትምህርት ቤቶች በተፈናቃዮች መጠለያነት መያዛቸውን ገልጿል::
በኢሮብ ወረዳ በአከባቢው የተፈጠረው ድርቅ ባስከተለው ረሃብ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ እያስገደደ መሆኑን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ኢያሱ ተስፋይ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል::