በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ታንዛንያ "ህገ-ወጥ ናቸው" ያለቻቸውን ከ80 በላይ ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር አዋለች


የታንዛንያ ካርታ
የታንዛንያ ካርታ

ኢዮጵያውያኑ በፖሊስ ቁጥጥር ስር በነበሩበት ጊዜ፣ ከረሃብና ከውኃ ጥም የተነሳ ሰዉነታቸዉ በጣም ተዳክሞ እንደነበረ የሃገሪቱ ፖሊስ አስታዉቀዋል። ባለሥልጣናት ለአሜርካ ድምጽ እንደተናገሩት፣ ሌሎች ህገ-ወጥ የተባሉ ኢትዮጵያውያንም በኬይላ ታንዛንያ እስር ቤት ዉስጥ ይገኛሉ።

"ህገ-ወጥ ናችሁ" የተባሉ ከ80 በላይ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች በዚህ ሳምንት መጀምሪያ በደቡብ ምሥራቅ ታንዛንያ ኢሪንጋ በምትባል ግዛት ዉስጥ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል። የአካባቢዉ ፖሊስ ኮማንደር ፒተር ካካምባ በወቅቱ ለጋዘጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ፍልሰተኞቹ በጭነት መኪና ተሳፍረው ይሄዱ እንደነበርና፣ ፖሊስ ይሄዱበት የነበረዉን መኪና አስቁሞ ባይታደጋቸዉ ኖሮ ከስደተኞቹ የበርካቶች ህይወት ማለፍ ይችል እንደነበረ ታውቋል።

በከባድ የጭነት መኪና ተፋፍገው ይሄዱ ከነበሩት ከእነዚሁ ህገ-ወጥ ከተባሉት ኢትዮጵያውያን መካከል ሦስቱ፣ በረሃብና በዉኃ ጥም ሰዉነታቸዉ በመዳከሙ፣ ወደ ሆስፒታል ተወስደው ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል። ከማላዊ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘዉ እምቤያ፣ ኢሪንግ በምትባል አከባቢ የተያዙት ኢትዮጵያዉያንም በማላዊ አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ ያመሩ የነበሩ መሆናቸዉንም ኮማንደሩ በመግለጫቸዉ አንስተዋል።

ፍልሰተኞቹ በአሁኑ ጊዜ ያሉበት ሁኔታ ባይታወቅም፣ የኬይላ ግዛት ኮምሽነር የሆኑት ዶክተር ቴሃ እንጋራ ግን፣ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን አስመልክተው፣ "እኛ የምናረገዉ እነሱን ወደ ፍርድ ቤት እንወስዳቸዋለን ከዚያም ወደ እስር ቤት እንድወሰዱ ይደረጋል" ብለዋል።

እንደ ዶክተር ቴሃ ንግግር፣ ህገ-ወጥ ስደተኞቹን በቁጥጥር ያዋሏቸዉ የኬይላ የኢሚግሬሽን ቢሮና የአካባቢዉ ፖሊስ ሲሆኑ፣ በዚህ ሳምንት ተያዙ ከተባሉት ከ80 በላይ ኢትዮጵያዉያን በተጨማሪም፣ ሌሎች የኢትዮጵያ ዜጎችም በኬይላ ታንዛንያ እስር ቤት ዉስጥ እንደሚገኙ ይናገራሉ።

"አዎን በእርግጥም በእስር ላይ ያሉ አሉ። የእስር ጊዜያቸዉን ሲጨርሱ፣ ሁሌም እንደምናረገዉ፣ ወደ ሃገራቸዉ እንልካቸዋለን። እና አሁንም ሌሎች እስረኞች በማረምያ ቤት ዉስጥ ያሉ አሉ። ለምሳሌ እኔ በማስተዳድረዉ ግዛት ዉስጥ የእስር ጊዜያቸውን በቅርቡ የሚጨርሱ በርካታ ሰዎች አሉ" ብለዋል።

ኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ ውስጥ የቆንስላ ቢሮ የላትም። እናም በቁጥጥር ስለዋሉት ኢትዮጵያውያን እስረኞች የኢትዮጵያ መንግሥት ጠይቋችሁ ያዉቃል ወይ? ብለን ላነሳንላቸዉ ጥያቄ፣ ኮምሽነሯ ይህን መልሰዋል።

"አይገባኝም። ምናልባት ግድ ስለሌላቸዉ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች ህጋዊ ሰነድ አግኝተው እንዲወጡ አልፈቀዱላቸዉምም ይሆናል፣ እስካሁንም ከእኛ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አላደረጉም" በማለት ገልጸዋል።

እንደተባለው ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ ውስጥ የቆንስላ ቢሮ የላትም። ይህን ዓይነቱን ጉዳይ የሚከታተለው ኬንያ ናይሮቢ የሚገኘዉ የቆንስላ ጽሕፈት ቤት በመሆኑ ወደዚያው ደውለን ጠየቅን። "ይህን ገና ከእናንተ ነዉ የሰማነዉ፣ ተከታትለን የደረስንበትን እናሳዉቃለን" ብለው ቃል ገብተውልን ነበር። ይህ ዜና እስከተቀነባበረበት ጊዜ ግን መልስ አላገኘንም። በቆንስላ ጽ/ቤቱ የዳያስፖራ ጉዳይ ምክትል ስራ አስፈጻሚ የሆኑትን አቶ አንዳርጉ በርሄን በተደጋጋሚ በስልክና በ ኢሜይል (e-mail) ለማግኘት ያደረግንው ሙከራም አልተሳካልንም።

የታሰሩትን ኢትዮጵያዉያን ማንነት ለማወቅ ለኬይላ ግዛት ኮምሽነር ለዶክተር ቴሃ ጥያቄ አቅርበን ነበር። "ማንነታቸዉን በግልጽ ባላዉቅም አብዛኛዉን ግዜ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ግዛታችን አቋርጠው የሚመጡት፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል የሆኑ ወጣቶ ናቸው" ብለውናል።

ኢትዮጵያዉያን ፍልሰተኞችን በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ታንዛንያ በማዘዋወር፣ አለክስ አዳም የሚባል የታንዛንያ ዜጋም በሃገሪቱ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሉን ተረድተናል። ከዚህ በፊት እአአ በሰኔ 2012 በሰሜን ማዕከላዊ ታንዛንያ ኮንጋ ተብላ የምትጠራ አካባቢ በህገ-ወጥ መንገድ የጭነት መኪና ታጉረው በመሄድ ላይ የነበሩ ቁጥራቸዉ ከ40 በላይ የሆነ ኢትዮጵያዉያን፣ በአየር እጦት ህይወታቸዉ እዚያው መክናው ውስጥ ማለፋ የምታወስ ነዉ።

ገልሞ ዳዊት ከናይሮቢ ጉዳዩን በቅርብ ተከታትሎ የላከውን ዘገባ ከድምጽ ፋይሉ ያድምጡ።

ታንዛንያ "ህገ-ወጥ ናቸው" ያለቻቸውን ከ80 በላይ ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር አዋለች
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:17 0:00

XS
SM
MD
LG