በሦርያው አለመረጋጋት የተጠመዱ ዋናዎቹ ኃይሎች፣ በጠላትነት ያለመተያየት ወይም ያለመፈራረጅ ስምምነት በሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደሚፈራረሙ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዦን ኬሪ አስታወቁ።
ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዛሬ ዐርብ ይህን ካስታወቁ በኋላ፣ በጠላትነት ያለመተያየቱ የሚውኒክ ስምምነት በተፈረመበት በጀርመኑ የተመድ የሰብዓዊ እርዳታ ስብሰባ ሊቀ-መንበር ጃን ኤግላንድ በበኩላቸው፣ ስንጠብቀው የነበረ ትልቅ እርምጃ ነው» ማለታቸው ተሰምቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሦርያ ሽምቅ ተዋጊዎች በሰጡት መግለጫ፣ ምዕራባውያን ገሸሽ ካደረጓቸው ወይም ተቀባይነት የሌለው የፖለቲካ ፍትሔ ለማቅረብ ከሞከሩ ፕሬዚደንት በሽር አል-አሳድን ለማስወገድ ያካሄዱትን የ5 ዓመት ትግል ወደ ህቡዕ እንደሚወስዱት አስጠነቀቁ።
የሽምቅ ተዋጊዎቹ ቡድን ጦር አዛዥና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በበኩላቸው፣ በአሳድ ገዥ መደብና "የውጪ ወራሪዎች" ባሏቸው ከኢራን እና ከሩስያ በመጡ ወገኖች ላይ ያላሰለሰ የደፈጣ ውጊያ እንደሚያደርጉ፣ ጦርነቱንም ወደ የነፃነት ውጊያ እንደሚቀይሩት አስታውቀዋል።