በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማሊያ ከቱርክ ጋራ የመከላከያ ስምምነት ፈጸመች


የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሃሳን ሼክ ሞሃመድ
የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሃሳን ሼክ ሞሃመድ

የሶማሊያ የካቢኔ እና የፓርላማ ዓባላት፣ ከቱርክ ጋር ለተፈጸመ የመከላከያ ስምምነት ዛሬ ረቡዕ ይሁንታቸውን ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ እንደራሷ ግዛት የምትቆጥራት ራስ ገዟ ሶማሊላንድ፣ ከአንድ ወር በፊት የባሕር በርን በተመለከተ የፈረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ፣ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ውዝግብ ውስጥ ቆይተዋል።

የ10 ዓመታት የተፈጻሚነት ዕድሜ አለው በተባለው ስምምነት፣ ቱርክ የሶማሊያን የባሕር ድንበር ለመከላከል እገዛ እንደምታደርግና የባሕር ኃይሏንም እንደገና እንደምትገነባላት፣ ከፓርላማው ስብሰባ በኋላ ለዜና ሰዎች የተናገሩት የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሃሳን ሼክ ሞሃመድ አስታውቀዋል።

“ዛሬ ለፓርላማው የቀረበው ስምምነት፣ በሶማሊያ እና በቱርክ መካከል ስለሚኖር የባሕር ላይ የመከላከያ ኃይልን እና ኢኮኖሚን የተመለከተ እንጂ፣ ከሌላ አገር ጋር ጥላቻንም ሁነ ሽኩቻ ለመፍጠር ያለመ አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል ፕሬዝደንቱ።

የባሕር በር የሌላት ኢትዮጵያ፣ ለወደብ እና ለባሕር ኃይሏ የሚውል ሥፍራ እንድታገኝ የሚያስችል ነው የተባለ የመግባቢያ ስምምነት፣ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት የመጀመሪያ ቀን፤ ከሶማሊላንድ ጋራ መፈረማቸውን ተከትሎ፣ ሶማሊያ አጥብቃ ተቃውሞዋን ስትገልጽ ቆይታለች፡፡

“ሶማሊያ አቋሟን ግልጽ አድርጋለች፡፡ የሶማሊያ ሉዐላዊነት እና የግዛት አሃድነት ለድርደር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። የዛሬው ታሪካዊ ስምምነትም በዚህ መሠረት የተፈጸመ ነው“ ሲሉ የሶማሊያው የመከላከያ ሚኒስትር አብዲፋታህ ቃሲም መናገራቸውን የኤኤፍፒ ዘግባ አመልክቷል።

“የሶማሊያን የባሕር ጠረፍ ለመከላከል ቱርክ ተመራጭ ናት” ሲሉ አክለዋል ሚኒስትሩ።

የኔቶ ዓባል የሆነችው ቱርክ ከሶማሊያ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ በተለይም በግንባታ፣ በትምሕርት እና ጤና ዘርፎች እንዲሁም በወታደራዊ መስክ ትብብር እንደምታደርግ ታውቋል።

ቱርክ በውጪ አገር ያላት ትልቁ ወታደራዊ መሠረትና ማሰልጠኛ በሶማሊያ እንደሚገኝ እንዲሁም 5ሺሕ የሚሆኑ የሶማሊያ መከላከያ ሠራዊት ዓባላትን ማሰልጠኗን የቱርክ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የሰለጠኑት ወታደሮች፣ በዚህ ዓመት መጨረሻ ተልዕኳቸው የሚያከትመውን የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይሎችን ከሚተኩት ውስጥ እንደሚሆኑ ተነግሯል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG