በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ የሶማሊላንዱን ስምምነት ካልሰረዘች ለድርድር እንደማትቀርብ ሶማሊያ አስታወቀች


የሶማሊያ ፕሬዚደንት ሃሰን ሼኽ መሀሙድ ከአስራ አምስት ቀናት በፊት ለፓርላማቸው ባደረጉት ንግግር “የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ስምምነት የሶማሊያን ሉዓላዊነትና ዓለምአቀፍ ህግን የሚፃረር ነው” ሲሉ አውግዘውታል።/ ፎቶ ፋይል/
የሶማሊያ ፕሬዚደንት ሃሰን ሼኽ መሀሙድ ከአስራ አምስት ቀናት በፊት ለፓርላማቸው ባደረጉት ንግግር “የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ስምምነት የሶማሊያን ሉዓላዊነትና ዓለምአቀፍ ህግን የሚፃረር ነው” ሲሉ አውግዘውታል።/ ፎቶ ፋይል/

ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ በቅርቡ የፈረሙትንና ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታገኝ የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ቀድመው ካልሰረዙ፣ ለድርድር እንደማትቀርብ ሶማሊያ ዛሬ ሐሙስ አስታውቃለች፡፡

የአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ዛሬ በለቀቀው መግለጫ፣ “ሕገ ወጥ” ሲል የጠራው የሁለቱ ወገኖች የመግባቢያ ስምምነት “ወድቅ ካልሆነ እና የሶማሊያን ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት መልሶ የሚያረጋግጥ ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ የሚደረግ ድርድር አይኖርም” ብሏል።

የሶማሊያ መግለጫ የመጣው፣ የአፍሪካ ኅብረት የጸጥታው ምክር ቤት፣ በሁለቱ ጎረቤት አገራት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት በተመለከተ ትናንት ረቡዕ መወያየቱን ተከትሎ ነው።

ም/ቤቱ ሁለቱ መንግሥታት ውጥረቱን አስወግደው ሰላማዊ መፍትሄ ለመሻት ትርጉም ያለው ውይይት እንዲያደርጉ ጠይቋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ልማት የበይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) በበኩሉ ዛሬ ሐሙስ ኡጋንዳ-ካምፓላ ላይ ልዩ ስብሰባ ጠርቷል፡፡ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት እና በሱዳን ያለውን ግጭት በተመለከተ እንደሚነጋገር ታውቋል።

በስብሰባው ላይ ኢትዮጵያ እንደማትካፈል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ቻይና፣ የዓረብ ሊግ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተዋንያን፣ የሶማሊያ የግዛት ሉአላዊነት እንዲከበር ጠይቀዋል።

ሞቃዲሹ የመግባቢያ ስምምነቱ በኢትዮጵያ የተፈጸመ “ጠብ ጫሪነት” ነው ስትል፣ ኢትዮጵያ በበኩሏ የተጣሰ ሕግ የለም ትላለች፡፡

ስምምነቱ አል ሻባብን እንዲያንሰራራ ያደርጋል ሲሉ የሶማሊያው ፕሬዚደንት ሃሳን ሼክ ሞሃመድ ማስጠንቀቃቸውንም የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።

የዐረብ ሊግ ዋና ጸሓፊ አሕመድ አቡል ጌት ትናንት ረቡዕ በተደረገው የዐረብ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አስቸኳይ ስብሰባ ላይ፣ የመግባባቢያ ሰነዱ፥ “በዓረብ፣ በአፍሪካውያንና በዓለም አቀፍ መርሖዎች ላይ የተቃጣ ግልጽ ጥቃት ነው፤” ሲሉ፣ አውግዘውታል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG