በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የባሕር በር ውል ቋጠሩ


ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የባሕር በር ውል ቋጠሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:46 0:00

ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የባሕር በር ውል ቋጠሩ

ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበት የመግባቢያ ሠነድ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መሪዎች ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ተፈርሟል።

ስምምነቱ ለ50 ዓመት የሚዘልቅ ሊዝ እና እየታደሰ የሚቀጥል መሆኑን የገለፁት የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን ኢትዮጵያ ሶማሌላንድ ውስጥ የጦርና የንግድ ሠፈር እንዲኖራት የሚፈቅድ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ወደ አደን ባሕረሰላጤ የባሕር በር ልታገኝ የምትችልበትን የመግባቢያ ሠነድ ዛሬ ታህሳስ 22 / 2016 ዓ.ም. አዲስ አባባ ላይ የፈረሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና እንደሃገር ዓለምአቀፍ ዕውቅና የሌላት የሶማሌላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዱ ናቸው።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፅህፈት ቤታቸው ውስጥ ከተከናወነው የፊርማ ሥርዓት በኋላ በሰጡት አስተያየት “ስምምነቱ ከኢትዮጵያ ጉልህ ስብራቶች መካከል አንዱን የሚጠግን ነው” ብለዋል።

ስምምነቱ ከኢትዮጵያ ጉልህ ስብራቶች መካከል አንዱን የሚጠግን ነው

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓርብ ጥቅምት 2 / 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲናገሩ ጥያቄው “የሕልውና ጉዳይ ነው” ብለው ነበር።

ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋን “በግድያና በጦርነት ማሳካት የለባትም” ብለዋል ያኔ። ጉዳዩ በድርድር እልባት ካላገኘ ወደፊት የግጭት መንስዔ ሊሆን እንደሚችልም አሳስበው “የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የጂቡቲና የሶማሊያ መሪዎች እንነጋገር” የሚል መልዕክትም አስተላልፈው ነበር።

ይህን ተከትሎ በተለይ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ውጥረት ውጥረት መሽተቱና መነጋገሪያ ሆኖ መቆየቱ ሲሰማ ሰነባብቷል።

የኤርትራ መንግሥት ጥቅምት 5 ባወጣው መግለጫ በቅርብ ጊዜ "ስለውኃ፣ ስለባሕር በርና ተዛማጅ ጉዳዮች" እየተሰሙ ያሉ ንግግሮች ከልክ በላይ ናቸው፤ ጉዳዩ “የሚመለከታቸውን ሁሉ ግራ አጋብቷል” ብሎ ነበር። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በቀጥታ ሳይጠቅስ “እንደዚህ ወዳሉ መንገዶችና መድረኮች ኤርትራ አትሳብም” ብሏል።

ሶማሊያና ጂቡቲ ደግሞ “ወደብን ጨምሮ የግዛታዊ አሃድነት ጉዳያቸው ለድርድር አይቀርብም” ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስም ከባሕር በር ጥያቄ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እየታየ ነው የሚባለው “ውጥረት እንደሚያሳስባት” ገልፃለች።

ጉዳዩ መነጋገሪያ መሆኑን ተከትሎ ኢትዮጵያ ጥያቄዋን በኃይል የማሳካት ፍላጎት እንደሌላት በተደጋጋሚ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዛሬው ስምምነትም ይህንኑ እንደሚያንፀባርቅ ተናግረዋል።

የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው ሬድዋን ሁሴን ከፊርማው በኋላ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ የባሕር በር ለማግኘት ከሌሎች ጎረቤት ሀገሮች ጋርም ውይይት ተደርጎ እንዳልተሳካ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ እንደ አየር መንገድ ያሉ ኩባንያዎቿን የባሕር በር ለማግኘት ለድርድር ማቅረቧን፣ ሶማሊላንድ በኢትዮጵያ ኩባንያዎች ውስጥ ሊኖራት ስለሚችለው ድርሻና ኢትዮጵያ ለባሕር በሩ ስለምትከፍለው ሊዝ ዝርዝር ውይይቶች እንደሚደረጉም ገልፀዋል።

ከሶማሊላንድ ጋር በተፈረመው የመግባቢያ ሠነድ ኢትዮጵያ የምታገኘው የባሕር በር በቦታና በመጠን መታወቁንም አምባሳደር ሬድዋን አመልክተዋል። ወደ ተግባር የሚያስገቡ ሌሎች ሂደቶች በአንድ ወር ውስጥ እንዲጠናቀቁ ስምምነት መደረሱንም አብራርተዋል።

ምንም እንኳ ዓለምአቀፍ ዕውቅና የሌላት ሶማሊላንድ ራሷን እንደ ሉዓላዊ ሀገር ብትቆጥርም የግዛቷ አካል እንደሆነች የምትናገረው ሞቃዲሾ በዛሬው ስምምነት በይፋ አስተያየት አልሰጠችም።

ይሁን እንጂ የሶማሊያ ካቢኔ ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ በፈረሙት ሠነድ ላይ ለመምከርና ውሣኔ ላይ ለመድረስ ነገ እንደሚሰበሰብ የሶማሊያ ብሄራዊ የዜና አገልግሎት (ሶና) ማምሻውን ኤክስ ላይ ባወጣ አጭር መረጃ አስታውቋል።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደ’ኤታ አሊ ኡመር ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በሰጡት ምላሽ "የሶማሊያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት፣ መሬት፣ ባህርና አየር ለድርድር አይቀርቡም” ብለው ነበር።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG